Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የጸጥታ ችግር ያጋጠማቸው አካባቢዎች የተለየ መቁረጫ ነጥብ ለመወሰን የሚያስገድድ የውጤት ትንተና ስላልተገኘ በመደበኛው የመቁረጫ ነጥብ ተስተናግደዋል- ትምህርት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 9 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የጸጥታ ችግር ያጋጠማቸው አካባቢዎች የተለየ መቁረጫ ነጥብ ለመወሰን የሚያስገድድ የውጤት ትንተና ስላልተገኘ በመደበኛው የመቁረጫ ነጥብ ተስተናግደዋል አለ የትምህርት ሚኒስቴር፡፡

የትምህርት ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ 12ኛ ክፍል የፈተና ውጤት እና የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥብ ጋር ተያይዞ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም የ12ኛ ክፍል ፈተና በሁለት ዙር እንዲሰጥ መደረጉንና በመጀመሪያው ዙር የስነ-ዜጋና ስነ ምግባር ትምህርት ከፈተናው ቀን ቀድሞ በመውጣቱና የውጤት ግሽበት በመምጣቱ እንዲሰረዝ መደረጉን አስታውሰዋል።

በመጀመሪያ ዙር ፈተና ከወሰዱት ተማሪዎች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት 50 ከመቶና ከዚያ በላይ ውጤት ማስመዝገባቸውን የተናገሩት ሚኒስትር ዲኤታው፥ በመጀመሪያው ዙር ፈተና ከወሠዱት 544 ሺህ 682 ተማሪዎች ውስጥ 44 ከመቶዎቹ 50 ከመቶ እና ከዚያ በላይ ውጤት ማስመዝገባቸውን አብራርተዋል።

በሁለተኛው ዙር ከተፈተኑት 53 ሺህ 997 ተማሪዎች ውስጥ 28 ከመቶዎቹ ወደ መንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የሚመደቡ ሲሆን ከመጀመሪያው ዙር 554 ሺህ 682 ተፈታኞች ውስጥ ደግሞ 25 ከመቶዎቹ ይመደባሉ ብለዋል።

የ10ኛ ክፍል የማትሪክ ፈተና በመቅረቱ ምክንያት በጣም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች በዘንድሮው አመት የ12ኛ ክፍል ፈተናን ወስደዋል ያሉት ሚኒስትር ዲኤታው÷ አራት ዩኒቨርሲቲዎች መቀበል በማይችሉበት ሁኔታ ከአምናው የተሻለ ቁጥር ያለው ተማሪ ወደ መንግስት ዩኒቨርሲቲዎች እንዲመደቡ መደረጉን አብራርተዋል።

በትግራይ ክልል ያሉ 4 ዩኒቨርሲቲዎች ይማሩ የነበሩ ተማሪዎች ወደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች መመደባቸውና ዘንድሮም ይመደቡ የነበሩ ተማሪዎች ወደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች እንዲመደቡ መደረጉ 48 ሺህ ተማሪ የቅበላ አቅም አጥተናል ብለዋል።

ነገር ግን ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመነጋገር በ43 የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች 152 ሺህ 14 ተማሪዎች እንዲመደቡ መደረጉና ይህም ከአምናው የቅበላ አቅም ጋር ሲነፃፀር ከፍ ያለ መሆኑን አስረድተዋል።

ባለፈው አመት በ47 ዩኒቨርሲቲዎች 147 ሺህ ተማሪዎች ምደባ የተደረገ ሲሆን÷ ዘንድሮ በ43 ዩኒቨርሲቲዎች 152 ሺህ 14 ተማሪዎች እንዲመደቡ መደረጉን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version