Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የብልጽግና ፓርቲ ተተኪ አመራሮችን ወደ ኃላፊነት በማምጣት ተራማጅነቱን በተግባር አሳይቷል-የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የብልጽግና ፓርቲ በዲሞክራሲያዊና ነጻ ምርጫ ተተኪ አመራሮችን ወደ ኃላፊነት በማምጣት ተራማጅነቱን በተግባር አሳይቷል ሲሉ የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ተናገሩ፡፡
የብልጽግና ፓርቲ ከሰሞኑ በአዲስ አበባ ባካሄደው የመጀመሪያ ጉባኤው የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፎ መጠናቀቁ ይታወቃል፡፡
በጉባኤ የፓርቲውን ፕሬዚዳንት ጨምሮ ሁለት ምክትል ፕሬዚዳንቶችን እንዲሁም የማዕከላዊና ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የተመረጡ ሲሆን÷ በዚህም ፓርቲው በርካታ ተተኪ አመራሮችን ወደ ኃላፊነት ማምጣቱ ተገልጿል፡፡
በጉባኤው የተካሄደውን ምርጫ አስመልክቶ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት እንደሚሉት÷ ጉባኤው በኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል አዲስ ዴሞክራሲያዊ ልምምድ የታየበት ነው፡፡
የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ግርማ የሺጥላ÷ በጉባኤው አንዱ ተመልካች ሌላኛው ደግሞ ወሳኝ ሳይሆን ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያለምንም ገደብ የፈለጉትን አካል መርጠዋል ብለዋል፡፡
የጉባኤው ተሳታፊዎች በብሔርና ክልል አጥር ሳይገደቡ ትክክለኛ ኅብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትን በተግባር ማሳየታቸውንም ነው ያነሱት፡፡
ሌላኛዋ የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ወይዘሮ አይናለም ንጉሴ በበኩላቸው÷ በጉባኤው የተካሄደው ምርጫ ፍጹም ዴሞክራሲያዊና ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች አርአያ የሚሆን ጭምር ነው ብለዋል፡፡
ጉባኤው አሳታፊ ከመሆኑም ባሻገር ለኢትዮጵያ ህዝብ በቀጥታ የተላለፈ መሆኑን ያስታወሱት ወይዘሮ አይናለም፥ ይህም ብልጽግና በኢትዮጵያ ሊያሳካው ለሚፈልገው አሳታፊ የዲሞክራሲ ስርዓት መሰረት የጣለ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡
ፓርቲው ውስጠ ድርጅት ዲሞክራሲያዊነትን በተግባር በማሳየት በኢትዮጵያ የሰለጠነ የፖለቲካ ምህዳር እንዲሰፍን አርአያ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
ፓርቲው ከምስረታው ጀምሮ በአመራር ግንባታ ላይ ያተኮሩ ተግባራትን እያከናወነ መምጣቱን ጠቀሰው÷ በጉባኤው ተተኪ ወጣት አመራሮችን ወደ ኃላፊነት በማምጣት ተራማጅነቱን አሳይቷል ነው ያሉት፡፡
ፓርቲው አዲሱን ትውልድ ልምድ ካለው ጋር በማጣመር ወደ ተሻለ ነገ ሊያሻግር የሚችል ጠንካራ የአመራር መስተጋብር መፍጠሩንም አንስተዋል፡፡
የአፈጻጸምና የስነ ምግባር ችግር ያለባቸው አመራሮች ላይ እርምጃ በመውሰድም ለሕግ የበላይነት መስፈን ያለውን ቁርጠኝነት ማሳየቱንም አብራርተዋል፡፡
የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላቱ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ የምርጫ ሂደትም አሳታፊና ትክክለኛ ኅብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት የተረጋገጠበት እንደነበር ነው ያነሱት፡፡
Exit mobile version