አዲስ አበባ ፣ የካቲት ፣ 2012(ኤፍ ቢ ሲ) የሃውቲ አማጽያን ትብብር ካላደረጉ አሜሪካ በየመን የምታቀርበውን ድጋፍ ልታቋርጥ እንደምትችል ገለፀች።
የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት የሀውቲ አማጽያኑ የእርዳታ ማጓጓዙን ማስተጓጎል ካላቆሙ በስተቀር ከመጋቢት ወር ጀምሮ የሰብዓዊ ድጋፉን እንደሚያቋረጥ ገልጿል።
ኤጀንሲው በሰሜን የመን ዕርዳታ እንዳይቀንስ የምንችለውን ሁሉ ማድረጋችንን እንቀጥላለን ብለዋል።
በየመን እየተካሄደ የሚገኘው የእርስ በርስ ጦርነት በአስር ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ህይወት መቀጠፍ ምክንያት ሲሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በረሃብ ስጋት ይገኛሉ።
ይህንንም ተከትሎ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የመን በዓለም ላይ እጅግ የከፋ የሰብአዊ ቀውስ የተጋረጠባት ሃገር መሆኗን ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው ፡፡
በሀገሪቱ ባለው የእርስ በርስ ጦርነት ከሶስት ሚሊየን በላይ ሰዎች መኖሪያ ቀያቸው ሲፈናቀሉ ፤ በኮሌራ ወረርሽኝ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወታቸው አልፏል።
በተጨማሪም ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ቢያንስ 2 ነጥብ 2 ሚሊየን ሕፃናት በከባድ የምግብ እጥረት እየተሰቃዩ መሆኑን ነው ኤጀንሲው የገለጸው ፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ አሜሪካ ባለፈው ዓመት ለየመን 700 ሚሊየን ዶላር የሚጠጋ ድጋፍ ማድረጓን ዘገባው አመልክቷል።
ምንጭ፡-አልጀዚራ