አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በርካታ ቁጥር ያላቸው የትግራይ ወጣቶች የሕወሓትን ግፍ እና በደል በመሽሽ ወደ አማራ ክልል እየገቡ እንደሆነ የዋግ ኸምራ ብሔረሰብ ዞን ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ገለጸ፡፡
ሽብርተኛው የሕወሓት ቡድን በትግራይ ሕዝብ ላይ የሚያደርሰውን መጠነ ሰፊ ጫና በመሸሽ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ የትግራይ ወጣቶች ወደ አማራ ክልል መግባት መጀመራቸውን የዋግ ኸምራ ብሔረሰብ ዞን ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ ኮሎኔል ጌታወይ ዘገየ ተናግረዋል።
በተያያዘ ዜና፣ ራሳቸውን “የአገው ብሔራዊ ሸንጎ” በማለት የሚጠሩና ከሕወሓት የሽብር ቡድን ጋር ሲሰሩ የነበሩ በርካታ ታጣቂዎች በሰላም እጃቸውን እየሰጡ መሆኑን ተጠቁሟል።
ኃላፊው ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወጣቶችን ጨምሮ ከመሐል ትግራይ እየፈለሱ የሚመጡ በርካታ ሰዎች ወደ ዞኑ በስፋት እየገቡ ይገኛሉ።
“ከትግራይ ክልል ወደ አማራ ክልል እየገቡ ካሉ ወጣቶች ÷ ከሽብር ቡድኑ የስልጠና ማዕከላት ከድተው እንደመጡ የሚናገሩ ወጣቶች አሉ” ያሉት ኮሎኔል ጌታወይ ፤ ምናልባት የጠላት ቡድንን ተልዕኮ ይዘው የመጡ ሊኖሩ ስለሚችሉ የማጣራት ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።
የጥፋት ተልዕኮ ይዘው ሊመጡ የሚችሉ ጸጉረ-ልውጦችን ለመለየት የሚያስችሉና ኅብረተሰቡን ያሳተፉ እንዲሁም እስከ ቀበሌ ድረስ የተዘረጉ የተለያዩ አደረጃጀቶች መኖራቸውም አስረድተዋል።
ከአካባቢው አመራርና ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ተፈናቃዮችን ለማስተዳደር እየተሠራ መሆኑንም አብራርተዋል።
እንደ ኮሎኔል ጌታወይ ገለጻ፣ ከአካባቢው የአገር ሽማግሌዎች፣ ከሃይማኖት አባቶችና ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በመቀናጀት በተሠሩ ሥራዎች ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ ከ160 በላይ ራሳቸውን “የአገው ብሔራዊ ሸንጎ” ብለው የሚጠሩና ከሕወሓት የሽብር ቡድን ጋር ግንኙነት የነበራቸው ታጣቂዎች እጃቸውን ሰጥተዋል።
ዞኑ በጥምር የፀጥታ ኃይሎች አማካኝነት ከወራሪ ቡድኑ ነፃ ከወጣ በኋላ እነዚህ ታጣቂዎች በሰላም እጃቸውን መስጠት በሚችሉባቸው ሁኔታዎች ዙሪያ ከፌዴራል እስከ ዞን ድረስ ባሉ የፀጥታ ተቋማትና የፖለቲካ አመራሮች ውይይት ተካሂዶ አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!