በክልሉ ህዝብ መሰረታዊ ሰብዓዊ ድጋፎች ፈጥነው እንዲደርሱ ለማድረግ ከቅርብ ቀናት ጀምሮ በየዕለቱ 40 ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ ክልል እንዲጓጓዙ የሚደረግ መሆኑንም ነው መንግስት ያስታወቀው።
መግለጫው እንዳመለከተው፥ ከትናንት ጀምሮ 17 ሰብዓዊ ድጋፍ የሚያደርጉ አጋር ድርጅቶች ክትባትን ጨምሮ የተለያዩ መድሃኒቶች፣ የህክምና ቁሳቁስና የምግብ አቅርቦት ወደ ትግራይ ክልል ማጓጓዝ እንደሚችሉ አረጋግጠዋል።
በዚህም መሰረት ሌሎች 11 አጋር ድርጅቶች በጭነት አውሮፕላን 257 ሺህ 192 ኪሎ ግራም መድሃኒቶች፥ የህክምና ቁሳቁስና የምግብ አቅርቦቶችን ከአዲስ አበባ ወደ መቀሌ ማጓጓዛቸው ተገልጿል።
ከ700 ሺህ ህዝብ በላይ እንዲፈናቀል እና ከአብኣላ በኩል ወደ መቀሌ የሚደረገው የሰብዓዊ አገልግሎት ጉዞ እንዲቋረጥ ያደረገውም፥ በአፋር ክልል ላይ ዳግም ወረራ ያካሄደው ሽብርተኛው የህወሓት ቡድን መሆኑ በግልጽ ሊታወቅ ይገባል ሲል መንግስት በመግለጫው አስገብዝቧል።
መንግስት የህዝቡን መብት ለማረጋገጥና በችግር ላይ ያሉትን ዜጎቹን ህይወት ለመታደግ ከማንም በላይ ሃላፊነት እንደሚሰማው ገልጾ፥ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ የሚላከው ሰብዓዊ ድጋፍ ለህዝቡ በቀጥታ እንዲደርስ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስቧል።
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ችግሩን በሚመጥን ደረጃ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ እንደሚጠበቅበት አመልክቷል።