አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሶማሊያ በአስር ዓመታት ውስጥ ሶስተኛው እና እጅግ አሰከፊ የተባለው ድርቅ እንዳጋጠማት ተገለጸ፡፡
በማዕከላዊ ሶማሊያ እና በደቡብ ሶማሊያ የሚገኙ መንደሮች በተከሰተው አስከፊ ድርቅ ክፉኛ የተጎዱ አካባቢዎች መሆናቸው ተመላክቷል።
በተለይ ሴቶች እና ህጻናት በድርቁ ምክንያት ለአደጋ የተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ሲሆኑ÷ ብዙዎች አካባቢያቸውን ለቀው እየተሰደዱ መሆኑን አፍሪካ ኒውስ በዘገባው አስነብቧል፡፡
በኪስማዮ አጠቃላይ ሆስፒታል የማቋቋሚያ ማዕከል የስራ ተቆጣጣሪ የሆነው ፈይሰል ኢብራሂም እንደሚሉት÷ በከተማዋ የተገነቡ አዳዲስ የህክምና ካምፖች መቋቋማቸውን እና በየዕለቱ ወደ ስድስት የሚጠጉ ታካሚዎች ይቀበላሉ፡፡
ነገር ግን ጀማሜ፣ ጂሊብ እና ቡአሌ በሚባሉ አካባቢዎች ለሚኖሩ ሰዎች ምንም ዓይነት የምግብ ድጋፍም ሆነ ህክምና እንደማያገኙ ነው የገለጹት፡፡
ይህ ቀጣይነት ያለው የተመጣጠነ ምግብ እጦት ከፍተኛ ቀውስ እያስከተለ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
በኪስማዩ የሚገኘው የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ቡድን አባል የሆኑት አብዲ ዳጋኔ በበኩላቸው÷ በአካባቢው የተከሰተው ድርቅ እና ሌሎች አስከፊ እና ሁኔታዎች ተስፋ አስቆራጭ ናቸው ብለዋል፡፡
ብዙ ሰዎች ወደ ማረጋጊያ ማዕከሉ ይመጣሉ፤የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ያለባቸውን ልጆች እያየን ነው፤ ነገር ግን በገጠሩ አካባቢ ያለው ሁኔታ ከዚህም የከፋ ሊሆን ይችላል ነው ያሉት፡፡
ከጥር ወር ጀምሮ በሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ ከ120 ሺህ በላይ ሰዎች ወደ ማቋቋሚያ ማዕከላት መግባታቸው ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!