አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር በአቶ ተፈሪ ፍቅሬ የተመራ የልኡካን ቡድን በጉምሩክ ኮሚሽን የተከናወኑ ሁለንተናዊ የለውጥ ስራዎችን በዛሬው እለት ተዘዋውሮ ተመልክቷል፡፡
በጉብኝቱ ማጠቃለያ አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ ተፈሪ ፍቅሬ፣ ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት የሚኖረው ቀጣይነት ያለው አስተማማኝ ገቢ ሲኖር መሆኑን ጠቅሰው ፣ ጉምሩክ ኮሚሽን አሁን እየተጓዘበት ያለው የለውጥ መንገድ የማይናወጥ ኢኮኖሚን ለመገንባት የሚደረገውን ሁለንተናዊ ጥረት እንደሚያግዝ አስረድተዋል፡፡
በኮሚሽኑ ምቹ የስራ ከባቢን የመፍጠር ሳይንስ (ኤርጎኖሚክስ) በተሟላ መልኩ መተግበሩን በጉብኝታቸው መገንዘባቸውን የጠቆሙት አቶ ተስፋየ፣ በኮሚሽኑ እየተተገበሩ ያሉት ዘመናዊ ቴክኖሎጅዎች፣ ሰብአዊ ልማት እና የአሰራር ማሻሻያዎች ለሌሎች መንግስታዊ ተቋማትም ጭምር ተሞክሮ የሚሆኑ ናቸው ብለዋል፡፡
የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ በበኩላቸው፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት ኮሚሽኑ በህብረተሰቡ ዘንድ የተሳለበትን የተበላሸ ገጽታ ለመቀየር በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል፡፡
የኮሚሽኑ አመራሮች እና ሰራተኞችም አመራር በተለዋወጠ ቁጥር የማይናወጥ ጠንካራ ተቋም ለመገንባት ያላሰለሰ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
”በኮሚሽኑ የተተገበሩ ሁለንተናዊ ለውጦች በተለይም ምቹ የስራ ከባቢን በመፍጠር ረገድ የተሰሩት ስራዎች ከየትኛውም ሀገር ተሞክሮ ያልተወሰዱ፣ ከለውጥ ጥማት እና ከማህበረሰቡ የለውጥ ፍላጎት የተወለዱ ናቸው” ብለዋል።
በጉብኝቱ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የአገልግሎቶች እና መልካም አስተዳደር ክትትል ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አለምጸሐይ ጳውሎስ እና ሌሎች የጽ/ቤቱ አመራሮች መገኘታቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡