አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና የኢትዮጵያ ሰላም ለማረጋገጥ እና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን እያደረገች ያለው ጥረት የሚደነቅ ነው ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ፡፡
ቃል አቀባዩ በዛሬው ዕለት በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ፥ የቻይና የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልክተኛ ሹ ቢንግ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጋር መወያየታቸውን አንስተዋል፡፡
አቶ ደመቀ የህዳሴውን ግድብ ወደ ጸጥታው ምክር ቤት ለመውሰድ የተደረገውን ሙከራ በማክሸፍ፣ ዓለም አቀፍ ጫናዎችን በመመከት እና በኮቪድ-19 ዘመቻ ላይ ቻይና ላደረገችው ድጋፍ ምስጋና ማቅረባቸውን ገልጸዋል።
ቻይና የኢትዮጵያ ሰላምን ለማረጋገጥ እና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን እያደረገችው ያለውን ጥረትም አድንቀዋል።
የአፍሪካ ሃገራት ለሰላምና ለልማት ቢተባበሩ ቻይና ፍላጎቱ እንዳላትና አገራቱን በመሰረተ ልማት ለማስተሳሰር ፍላጎት እንዳላት እና ለዚህም ዝግጁ መሆኗ ተመላክቷል።
የኢትዮጵያ-ቻይና- አፍሪካ ሁለተኛው የፖለቲካ ምክክር ፎረም መካሄዱን ያስታወሱት ቃል አቀባዩ፥ በዚህም የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት በተለያዩ መስኮች ማጠናከር በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ ምክክር ተደርጓል ነው ያሉት።
በሌላ በኩል አዳዲስ አምባሳደሮች በጃፓን፣ አሜሪካ፣ ኩባ፣ ግብፅ፣ ሞሮኮ፣ ደቡብ ኮሪያ እና በሌሎች ሀገራት መሰማራታቸውን ጠቁመዋል፡፡
100 ሺህ የሚጠጉ ዜጎችን ወደ ሃገር ውስጥ ለመመለስ እየተሰራ ካለው ጥረት ጋር ተያይዞ 35 ሺህ ዜጎች ለመመለስ መመዝገባቸውንም አምባሳደር ዲና ተናግረዋል፡፡
በወንድወሰን አረጋኸኝ እና ምንችል አዘዘው