የሀገር ውስጥ ዜና

የኃይል ስርቆት ሲፈፅሙ የተገኙ ግለሰቦች ተያዙ

By Meseret Awoke

March 17, 2022

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የኤሌክትሪክ ኃይል ስርቆት ሲፈፅሙ የተገኙ 11 ተጠርጣሪዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሆነ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገለጸ፡፡

በከተማዋ በተለምዶ ሽሮሜዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በጥቃቅንና አነስተኛ ማህበር በተደራጀ አንድ ማዕከል ውስጥ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ የኤሌክትሪክ ኃይል ስርቆት ሲፈፅሙ የተገኙ 11 ተጠርጣሪዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን በአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኢነርጂ ማኔጅመንት ሥራ አስኪያጅ አቶ አስናቀው ፀሐይ ተናግረዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት መጋቢት 2 ቀን 2014 ዓ.ም የአገልግሎቱ ኢነርጂ ማኔጅመንት ቢሮ የኢንስፔክሽን ባለሙያዎች በአካባቢው ከሚገኙ የፖሊስ አካላት ጋር በመተባባር ባደረጉት ድንገተኛ የፍተሻ ስራ ሲሆን ፥ ግለሰቦቹ ከተፈቀደላቸው የኃይል መጠን ውጭ ሲጠቀሙ መገኘታቸውን ሥራ አስኪያጁ ገልፀዋል፡፡

የኃይል ስርቆቱን የፈፀሙት እነዚህ ተጠርጣሪዎች ፥ በአካባቢው በጥቃቅንና አነስተኛ ማህበር ተደራጅተው እንጀራ በመጋገር ስራ ላይ የተሰማሩ መሆናቸውንም ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

በተደረገው የማጣራት ስራም 1 ሚሊየን 65 ሺህ 889 ነጥብ 27 ኪ.ዋ.ሰ ኃይል መሰረቁንና በገንዘብ ሲተመን 2 ሚሊየን 263 ሺህ 948 ብር ከ80 ሣንቲም የሚደረስ ስርቆት መፈፀሙን አቶ አስናቀው አስታውቀዋል፡፡ በአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሕግ አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ታሪኩ ማዕረጉ በበኩላቸው ፥ ከተፈቀደለት የኃይል አጠቃቀም ውጭ ሲጠቀም የተገኘ ማንኛውም ግለሰብ በኢትዮጵያ የኢነርጂ አዋጅ ቁጥር 810/2006 መሰረት በህግ ተጠያቂ እንደሚሆን ገልፀዋል፡፡

ስለሆነም ህብረተሰቡ መሰል ድርጊቶችን ሲመለከት በአካባቢው ለሚገኝ የፀጥታ አካልና በአካባቢው ለሚገኝ የተቋሙ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት በአካል በመቅረብ ጥቆማ ሊሰጥ ወይም በ905 ነፃ የጥሪ ማዕከል በመደወል ሊያሳወቅ ይገባል ማለታቸውን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!