አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሚዛን አማን ከተማና አከባቢው የሥራ ጉብኝት አድርገዋል፡፡
ሚኒስትሯ ጉብኝታቸውን አስመልክተው በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ÷ “በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ የሚዛን አማን ከተማና አከባቢው የተመለከትኩት እምቅ ተፈጥሯዊ ውበት፣ የህዝቡ ሠው ወዳድነት እና አርቆ አሳቢነት የቱሪዝም አቅም ቀጣይ የኢትዮጵያ ተስፋን በግልጽ የሚያመላክት ነው” ብለዋል፡፡
ዲጋም ይስታዴ( ቤንችኛ) ጃጅቴ( ሸኮኛ) ዋማ ዲጎና ዋቶቴ (ከፍኛ) ሸኢሶ (መኤኒተኛ) ጄሺ (ዲዘኛ) አቻሊ (ሱርምኛ) ለመላው የሀገሬ ልጆች ክብር፣ ፍቅርና ስኬት ይገባችኋል ሲሉም አመስግነዋል፡፡
በተያያዘ ዜና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በከተማ ልማት ሚኒስቴር የከተሞች ተቋማዊና መሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም በክልሉ ለሚገኙ ለሶስት ከተሞች አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ሰልጠና ተሰጥቷል፡፡
በመድረኩ የተገኙት ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ ህዝቡ ከመንግስት የሚጠብቀውን የመልማት ፍላጎት እና ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ አመራሮች ሌት ተቀን መስራት ይገባቸዋል ብለዋል።
በመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች የከተሞችን አቅምን ለመገንባት በሚያስችሉ ስራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ በመስራት ከተሞችን ማልማትና ህዝብን በሚፈልገው መልኩ ማገልገል እንደሚኖርባቸዉ ተናግረዋል፡፡