አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 7 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያን የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ያለውን አማራጭ የኢንቨስትመንት ዕድል የሚያስተዋውቅ የኢንቨስትመንት ፎረም ለተባበሩት አረብ ኢሚሬቶችና ለውጭ አገራት ባለሃብቶች በዱባይ ተካሄዷል።
በፎረሙ ላይ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ምክትል ኮሚሽነር አቶ ተመስገን ጥላሁን ባደረጉት ንግግር÷ የዘርፉን የኢንቨስትመንት አማራጭ ለማስፋት መንግስት ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የውጭ ባለሀብቶችን ለመሳብ በርካታ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እየተገነቡ መሆናቸውን በተለይ በኦሮሚያ ቡልቡላ እና በሲዳማ ይርጋለም የተገነቡት ፓርኮች ስራ መጀመራቸውን አብራርተዋል።
መንግስት አገር አቀፉን ለውጥ ተከትሎ የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚው ውስጥ ትልቅ ሚና እንዲኖረው በማሰብ÷ የአገር በቀል የኢኮኖሚ ፖለሲን ጭምር የተለያዩ ባለሃብቶችን የሚያበረታታ እርምጃዎችን ተግባራዊ ማድረጉንም አክለዋል፡፡
በዘርፉ የውጭ ባለሀብቶች ከአገር ውስጥ ባለሀብቶች ጋር በሽርክና መስራት እንደሚችሉ መገለጹን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
በፋርማሲዩቲካልና ጤና እና በግብርና ማቀነባበር ኢንዱስትሪ ዘርፎች በተካሄዱ ፎረሞች በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች እና ለውጭ አገራት ባለሀብቶች ግንዛቤ ማስጨበጥ ተችሏልም ነው የተባለው።