Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ሚኒስቴሩ እያካሄደ ያለው መዋቅራዊ ማሻሻያ በቅርቡ ወደ ትግበራ እንደሚገባ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እያካሄደ ያለው የተቋሙ መዋቅራዊ ማሻሻያ ተጠናቆ በቅርቡ ወደ ትግበራ እንደሚገባ አስታወቀ።
 
በቅርቡ ምደባ ከተሰጣቸው አምባሳደሮች የተወሰኑት ወደ ተመደቡበት አካባቢ ሳይሄዱ በአገር ውስጥ ሆነው እንዲሰሩ ኃላፊነት እንደተሰጣቸውም ገልጿል።
 
ኢትዮጵያ የዜጎቿን መብትና ብሔራዊ ጥቅም እንዲሁም የኢኮኖሚ፣ ፖለቲካና ዲፕሎማሲ ጥቅሞች የሚያስከብር የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ እያራመደች እንደምትገኝ የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናግረዋል፡፡
 
ፖሊሲው በተለይ በንግድ፣ኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ዘርፍ፣ በአገር ሉዓላዊነትና ገፅታ ግንባታ፣ የኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን መብት ማስከበር ላይ ያተኮረ መሆኑንም ነው የገለጹት።
 
ዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊና ሀገራዊ ለውጦችን ታሳቢ ያደረገ ዘርፈ ብዙ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ትግበራ ላይ መሆኗንም አብራርተዋል።
 
የኢኮኖሚ ልማት፣ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እና አገራዊ መግባባትን በመፍጠር ብሔራዊ ጥቅምን የማስከበር ፖሊሲን የሚያግዙ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውንም አመላክተዋል።
 
 
መዋቅራዊው ማሻሻያ በቅርቡ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ወደ ትግበራ እንደሚገባ የጠቆሙት ቃል አቀባዩ፥ ወደ ፊት ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን ያገናዘበ ማሻሻያ ሊደረግበት እንደሚችልም ጠቁመዋል።
 
በምደባው የተካተቱ የተወሰኑ አምባሳደሮች ወደ ተመደቡበት አካባቢ ሳይሄዱ በአገር ውስጥ ሆነው የኢትዮጵያን ፍላጎትና ጥቅም ለማስከበር እንዲሰሩ ኃላፊነት እንደተሰጣቸው መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
 
በተወሰኑ አካባቢዎች ያሉ ኤምባሲዎች ደግሞ በአነስተኛ የሰው ኃይል ሰፊ አካባቢዎችን ተደራሽ እንዲያደርጉ አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸዋል።
Exit mobile version