አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የተከሰተውን የዘይት ዋጋ ንረት ለማረጋጋት ከውጭ የተገዛ 12 ነጥብ 5 ሚሊየን ሊትር ዘይት ወደ ሀገር ውስጥ ማጓጓዙን የኢትዮ-ጂቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር አስታወቀ፡፡
የማህበሩ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ጥላሁን ሳርካ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት፥ የገንዘብ ሚኒስቴር ከውጭ የገዛውን ዘይት በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሀገር ውስጥ አጓጉዞ ለማስገባት በተቀላጠፈ ሁኔታ እየተሰራ ነው፡፡
እስካሁንም ከውጭ ከተገዛው ዘይት ውስጥ 12 ነጥብ 5 ሚሊየን ሊትር ዘይት ወደ ሀገር ውስጥ አጓጉዞ ማስገባት መቻሉን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ውስጥም በሁለት ዙር 4 ነጥብ 8 ሚሊየን ሊትር ዘይት በባቡር ከወደብ ወደ አዲስ አበባ ተጓጉዞ እየተራገፈ መሆኑን ነው ዋና ዳይሬክተሩ የገለጹት፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በዛሬው ዕለት በሰጡት መግለጫ፥ በሚቀጥሉት 3 ወራት 150 ሚሊየን ሊትር ዘይት ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚገባ መግለጻቸው ይታወሳል።
በመላኩ ገድፍ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!