አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአረርቲ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚገኘው የሴራሚክ ፋብሪካ በሶስት ወራት ውስጥ ወደ ስራ ለማስገባት የሚያግዝ ምክክር ተካሂዷል፡፡
የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጅነር ታከለ ኡማ፣ የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ጌታቸው ጀምበር እና የፋብሪካው የስራ ኃላፊዎች የሴራሚክ ፋሪካው ያጋጠሙት ችግሮች ተፈትተው ወደ ስራ በሚገባበት ዙሪያ ተወያይተዋል።
ኢንጂነር ታከለ ኡማን ጨምሮ ሌሎች የመንግስት የስራ ኃላፊዎችን ያካተተ ልዑክ በአማራ ክልል የምንጃር ሸንኮራ ወረዳ አረርቲ ከተማ ኢንዱስትሪ ፓርክን የሚገኙትን የሴራሚክ ፋብሪካ፣ የጨርቃ ጨርቅ እና የእንጨት ፋብሪካዎች ጎብኝቷል፡፡
በዚሁ ወቅት የኢንዱስትሪ ፓርኩ በዋናነት ባጋጠመው የኤሌክትሪክ ችግር ካለፈው ዓመት የግንቦት ወር ጀምሮ ስራ ማቆሙ ተነግሯል።
በተመሳሳይ በቻይና ኩባንያ የሚተዳደረው የሴራሚክ ፋብሪካ ስራ ከጀመረ በኋላ በኃይል እጥረት እና በሌሎችም ምክንያቶች ሰራተኞችን በትኖ ከሥራ ውጭ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በዚህም በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ስራ ያቆመውን የሴራሚክ ፋብሪካ ወደ ስራ እንዲገባ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡
በውይይቱ ወቅት ኢንጅነር ታከለ ኡማ እንደገለጹት÷ ፋብሪካው ዕለታዊ የማምረት አቅሙ 20 ሺህ ሜትር ስኩዌር ሴራሚክ ነው።
ይሁን እንጂ ይህ ግዙፍ ፋብሪካ ምርቱን ለመቀጠል የኤሌክትሪክ ኃይልና የግብዓት እጥረት እያጋጠመው መሆኑን በጉብኝታችን ተረድተናል ብለዋል፡፡
ፋብሪካው በሶስት ወራት ውስጥ ያሉበት ችግሮች ተቀርፈው ወደ ምርት እንዲገባና ምርቱን ለገበያ ማቅረብ እንዲጀምር አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡
ሌሎች የተነሱ ችግሮችን ከክልሉ መንግስት ጋር በጋራ በመስራት መፍትሄ እንደሚሰጥም ጠቁመዋል።
በተመሳሳይ ልዑኩ ግንባታው ተጠናቆ እና ተጨማሪ ማሻሻያዎች ተጨምረውለት ወደ ግንባታ ለመግባት በዝግጅት ላይ ያለውንና በቢሾፍቱ ከተማ የሚገኘውን ካም የሴራሚክስ ፋብሪካ የጎበኘ ሲሆን÷ ቀሪ ስራዎችን በማጠናቀቅ ወደ ስራ ለማስገባት እንደሚሰራ ተመላክቷል፡፡
በለይኩን ዓለም
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!