አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቡና ባንክ እና በቡና ስፖርት ክለብ መካከል በ2013 ዓ.ም የተፈረመውና የመቆያ ጊዜው የተጠናቀቀው የዘላቂ አጋርነት ስምምነት እንዲራዘም ስምምነት ላይ በመደረሱ ለአንድ ዓመት ታድሷል።
ስምምነቱ በቡና ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉጌታ አለማየሁ እና በቡና ስፖርት ክለብ ፕሬዚዳንት አቶ ክፍሌ አማረ ተፈርሟል፡፡
በስምምነቱ መሰረት ቡና ባንክ ለኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብና ለክለቡ ደጋፊዎች ማህበር ለአንድ ዓመት የሚቆይ የአምስት ሚሊየን ብር ድጋፍ ያደርጋል።
ቡና ባንክ ለኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ እና ለስፖርት ክለቡ ደጋፊዎች ስኬትን እየተመኘ የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ዘላቂ አጋር በመሆኑ ክብር የተሰማው መሆኑን አብራርቷል።
ቡና ባንክ በቅርቡ በተፈረመ ስምምነት መሰረት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ስፖንሰር መሆኑንም ከባንኩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።