ቴክ

የተቋማት የማህበራዊ ትስስር ገጾች የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነት ለምን ጨመረ?

By ዮሐንስ ደርበው

March 15, 2022

 

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ተቋማት መረጃዎችን፣ አዳዲስ ሁነቶችን፣ ክስተቶችን እና ልህቀቶችን ለማስተዋወቅ እንዲሁም አገልግሎቶትን ለተጠቃሚዎች ለማድረስ የማህበራዊ ትስስር ገጾችን ይጠቀማሉ።

በኢትዮጵያ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ ካሉ የማህበራዊ ትስስር ገጾች መካከል÷ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ቁጥር ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል።

የማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎች፣ ተቋማት እና ግለሰቦች ብዙ ቁጥር ያላቸው ተከታዮችን በቀላሉ ማፍራትም ችለዋል።

በተቋማት ደረጃ የሚከፈቱ የማህበራዊ ትስስር ገጾችን ለማስተዳደር የተለያዩ የሚዲያ አድሚኖች እና ኤዲተሮች ገጹን እንዲያስተዳድሩና ይዘቶችን አበልጽገው እንዲለጥፉ ፍቃድ ይሰጣሉ።

የፌስቡክ አካውንት ባለቤቶች እና የፌስቡክ ገጽ አድሚኖች እንዲሁም ኤዲተሮች በመረጃ መንታፊዎች ኢላማ ውስጥ ሊወድቁ ይችላሉ።

አድሚኖች እና ኤዲተሮች ባለማወቅም ሆነ በቸለልተኝነት ማንነቱ ካልታወቀ ሰው ጋር ጓደኝነት በመፍጠር ወይም ከተጠቃሚ ክህሎት (ገጹን ከሚያስተዳደረው) አካል ክፍተት የተነሳ ገጾቹ ለተለያዩ እና ለረቀቁ የሳይበር ጥቃቶች ሲጋለጡ ይስተዋላል።

ገጹን እንዲያስተዳደሩ ፈቃድ የተሰጣቸው አካላትም ለጥቃት ከመጋለጣቸው በፊት ለሳይበር ጥቃት እንዲጋለጡ የሚያደርጓቸውን ስህተቶች ሊሰሩ ይችላሉ፡፡

በኢ-ሜይል አማካኝነት በሚላክ የመረጃ ማጥመጃ ዘዴ አማካኝነት የይለፍ-ቃል እና የዩዘር ኔም ስርቆት በመጋለጥ፣ ባልጠረጠርነው መንገድ ሽልማት ሰጪ፣ የስራ እድል ፈጣሪ፣ እርዳታ አቅራቢ መስለው በሚመጡ አካላት የይለፍ ቃሎችን ተጋላጭ ማድረግ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በአጭር የጽሁፍ መልዕክት የሚላኩ የአንድ ጊዜ የማረጋገጫ ኮዶችን አሳልፎ ለሌላ አካል መስጠት፣ ባለማወቅ እና ያለ ጥንቃቄ በኮምፒውተሮች እና በስልኮች ላይ ተንኮል አዘል ተልዕኮ ያላቸውን መተግበሪያዎችን መጫን፣ የጎግል አካውንት መለያን የመረጃ ማፈላለጊያዎች ላይ በማስቀመጥና አገልግሎቱን ሲጨርሱ ገጹን ሳይዘጉ መተውም ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭ ያሚያደርጉ ናቸው፡፡

በገጹ አስተዳዳሪ ወይም የኤዲተር ሚና ባለው ሰራተኛ ወይም አባል በኩል የፌስቡክ ገጾች የጥቃት ሰለባ ሊሆኑ እንደሚችሉ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ተቋማት ሊሰነዘርባቸው ከሚችሉ የሳይበር ጥቃቶች ራሳቸውን ለመከላከል ከላይ ተጠቀሱትን ተጋላጭነቶችን ማስወገድና ጥንቄቄ ማድረግ ይኖርባቸዋልም ተብሏል፡፡