የሀገር ውስጥ ዜና

የብልፅግና አንደኛ ጉባኤ ጥቅልና ጥልቅ በሆነው መሪ ሀሳብ መሰረት ውሳኔዎችና ቀጣይ አቅጣጫዎች የተቀመጡበት ነው – አቶ ደመቀ መኮንን

By Feven Bishaw

March 15, 2022

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የብልፅግና አንደኛ ጉባኤ ጥቅልና ጥልቅ በሆነው “ከፈተና ወደ ልዕልና” መሪ ሀሳብን መሰረት ያደረጉ ውሳኔዎችና የቀጣይ አቅጣጫዎች የተቀመጡበት ነው ሲሉ የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ደመቀ መኮንን ተናገሩ፡፡

የብልፅግና ፓርቲ አንደኛ ጉባኤ መጠናቀቅን አስመልክቶ የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት እና የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸው የብልፅግና አንደኛ ጉባኤ ጥቅልና ጥልቅ በሆነው ከፈተና ወደ ልዕልና መሪ ሀሳብን መሰረት ያደረገ ውሳኔዎችና የቀጣይ አቅጣጫዎች የተቀመጡበት ነው ብለዋል።

ጉባኤው በትኩረት የተወያየባቸው አገራዊ ተግዳሮቶች መኖራቸውን ያወሱት አቶ ደመቀ፥ ጠንካራ የድርጅት መዋቅር አለመኖር፣ ሌብነት፣ የአገልጋይነት መንፈስ አለመላበስ፣ የሰላም ዕጦትና አለመረጋጋት ላይ በጉባዔው ውይይት የተደረገባቸው መሆኑን ጠቅሰዋል።

ድርቅ፣ የዜጎች ሞት፣ መፈናቀልና ስደት፣ የውጭ ጣልቃ ገብነት በመሳሰሉ ተግዳሮቶች ላይ ሰፊ ውይይት መደረጉንም አንስተዋል።

አቶ ደመቀ አያይዘውም በፈተና ውስጥ የተገኙ ስኬቶችን የገለጹ ሲሆን የፖለቲካ ፣ የህግና የኢኮኖሚ ሪፎርሞችን ማድረግ፣ ታላቁ የህዳሴ ግድብና የስኳር ፕሮጀክቶችን የመሳሰሉ ትልልቅ አገራዊ ፕሮጀክቶችን አጠናቆ ወደ ምርት እንዲገቡ ማስቻል እንደ አገር የተገኙ ውጤቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ከውስጥና ከውጭ የሚደርሱ ጫናዎችን ተቋቁሞ መሻገር መቻል፣ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ ማድረግ እንዲሁም የፓርቲው የመጀመሪያ ጉባኤ በስኬት ማጠናቀቅ መቻል አገራዊ ድሎች ተደርገው መወሰዳቸውን አብራርተዋል፡፡

ፓርቲውን በሚገባ ማጠናከር፣ የሰላም እጦትና ስጋትን የሚፈታ አገራዊ ስርዓት መፍጠር፣በልዩ ልዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉና የተጎዱ ዜጎችን መልሶ ማቋቋምና በቂ ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግ፣ለፈተናዎች የማይበገሩ ብቁ አመራሮችን መፍጠርና ስምሪት ማድረግ፣ የአገራችንን ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር ከዚሁ ጋር ተያይዞ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ስራ መስራት በቀጣይ ትኩረት የሚሰጣቸው አቅጣጫዎች መሆናቸውን ነው ምክትል ፕሬዚዳንቱ የገለጹት፡፡

እንዲሁም ጉባኤው የለውጡን አራት አመታትና የፓርቲውን የሁለት ዓመታት ጉዞን በጥልቀት ባካሄደው ግምገማ የገጠሙ ፈተናዎችና አዎንታዊ ተሞክሮች ተለይተዋል ብለዋል።

ከገጠሙ ፈተናዎች መካከል የረጅም ጊዜ የፖለቲካ ቁርሾ፣ ሌብነት፣ ብልሹ አሰራር፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር፣ የሰላም እጦትና አለመረጋጋት፣ የውጪ ጣልቃ ገብነት፣ ወጀቡ የበዛ የሚዲያ ፍላጎትና ዘመቻ፣ የኑሮ ውድነትና ሌሎችም ተነስተዋል።

ባጋጠሙ ችግሮች ውስጥ በተሰሩ ሥራዎች ችግሮችን መቋቋም የሚችል አቅም መፍጠርና የተሻሉ ውጤቶችን ማስመዝገብ መቻሉ እንደ ስኬት የሚነሱ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ከፖለቲካ አንፃር ለ16 ዓመታት ተሞክሮ ሳይሳካ የቀረውን ውህድ ፓርቲ መመስረት፥ አዲስ የፓርቲ አደረጃጀትና አሰራር መዘርጋት መቻሉን ጠቅሰው፥ ከልማት አንፃርም ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ወደ ውጤት በማምጣት ረገድ የስኳር ፋብሪካዎቸና ህዳሴ ግድብ ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል፡፡

አቶ ደመቀ መኮንን በፈተናዎች ውስጥ የታለፈበትን ስኬታማ መንገድ ጠቅሰው÷ የህዳሴ ግድብ ሥራ እንዲቋረጥ ሰፊ ጫናዎች እንደበሩ ነው ያብራሩት።

ከዚህ ውስጥ ሰላም እንድታገኙ የግድብ ግንባታውን አቁሙ የሚል ኃይል እንደነበርም አስታውሰዋል።

ከውጪና ከውስጥ የተቀነባበሩና ግንባር የገጠሙ ኃይሎችን ጥፋት በብዛት ማክሸፍ የተቻለ ሲሆን÷ አሁንም ጠንካራ ስራ ይጠይቃል ነው ያሉት።

አሁን የቆምንበት መድረክ ያለፈውን የምንወቅስበት ሳይሆን፥ እኛም የታሪክ ተጠያቂ እንዳንሆን ያለፉ ጥፋቶች እንዳይደገሙ መስራት ላይ መሰረታዊ አቅጣጫ ተቀምጧል ነው ያሉት አቶ ደመቀ መኮንን በመግለጫቸው፡፡

በኃይለኢየሱስ ስዩም

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!