Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ብልጽግና ፓርቲ አመራሩን በየጊዜው እየገመገመ ሊጠየቅ የሚገባውን ለይቶ እርምጃ በመውሰድ ህዝብ የጣለበትን ሃላፊነት ሊወጣ ይገባል- ምሁራን

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ብልጽግና ፓርቲ አመራሩን በየጊዜው እየገመገመ የሚሸለመውን እና ሊጠየቅ የሚገባውን በትክክለኛ መንገድ እየለየ ህዝብ የጣለበትን እና የራሱን ቃል ሊጠብቅ ይገባል ሲሉ ምሁራን ገለጹ፡፡
 
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት በዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ጉዳዮች ተመራማሪ በቀለ ሀብታሙ፥ አሁን ሃገር ካለችበት የኑሮ ውድነት፣ የሰላም እጦት፣ ሌብነት እና ሌሎች ችግሮች ለመላቀቅ እንደ ከዚህ ቀደሙ አውርቶ ከመጥፋት ባሻገር በተግባር የሚታዩ ስራዎች ያስፈልጋሉ ብለዋል።
 
የጸጥታ እና የኑሮ ውድነት ችግርን ለመቅረፍም መንግስት በመዋቅሩ ውስጥ የተደበቁ ሙሰኛ የስራ ሃላፊዎች እና ሃላፊነት የማይሰማቸው የግል ባለሃብቶች የመሰረቷቸውን ህገ ወጥ ግኑኝነቶች ተከታትሎ መበጣጠስ ይገባል ብለዋል።
 
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ረዳት ፕሮፌሰሩ አንዳርጋቸው ተስፋሁን በበኩላቸው÷የኑሮ ውድነቱ የኢኮኖሚ ደረጃን መሰረት ባደረገ እና የዓለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታዎችን ከግንዛቤ ባስገባ መልኩ እልባት ሊበጅለት እንደሚገባ አንስተዋል።
 
የሚስተዋለው የጸጥታ ችግር ግን የመንግስትን ቁርጠኝነት እንደሚጠይቅ ነው ያብራሩት።
 
አመራሩ በየጊዜው እየተገመገመ የሚሸለመው እንዲሸለም እንዲሁም ተጠያቂ መሆን የሚገባቸውም እንዲጠየቁ የሚያደርጉ አሰራሮችም ሊኖሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
 
የጋራ በሆነች ሃገር ደግሞ ሁሉም ለውጥ ከአንድ ወገን ብቻ ይመጣል ብሎ ከመጠበቅ እሳቤ ተላቆ ጉዳዮችን የጋራ በማድረግ አብሮ ሊሰራ ይገባልም ብለዋል።
 
መንግስትም የህዝቡን ስሜት እና ፍላጎቶች የሚሰማባቸውን መንገዶች በማስፋት ይበልጥ ወደ ህዝብ መቅረብ እንዳለበትም ምሁራኑ አመላክተዋል።
 
ጥቃቅን ነገሮችን ከማጉላት በላይ ዋና ዋና ነገሮች ላይ ትኩረት በማድረግ በጋራ መረባረብ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡
 
በአፈወርቅ አለሙ
 
 
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version