Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

አቶ ደመቀ መኮንን ከቻይና የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ዙ ቢንግ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ዙ ቢንግ በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት አድርገዋል፡፡

በኢትዮጵያ ቆይታቸውም ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም በአገራቱ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው መንገዶች እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የቆየ ግንኙነት እና ቻይና ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ሁለገብ ድጋፍ አድንቀዋል።

በዚህ ረገድ ቻይና በባለብዙ ወገን መድረኮች ያደረገችውን ድጋፍ ኢትዮጵያ በሉዓላዊነቷ እና በግዛት አንድነቷ ላይ የተደቀኑ አደጋዎችን እንድታከሽፍ የረዳችውን ጠቅሰዋል።

ቻይና በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአፍሪካን ችግሮች ለመፍታት የአፍሪካን መርሆ መሠረት በማድረግ የወሰደችው ገንቢ አቋም እና ከኮቪድ-19 ጋር የተያያዙ ድጋፎች ሁሉ የሚደነቁ ናቸው ሲሉ አቶ ደመቀ ጨምረው ገልፀዋል።

ቻይና ለአፍሪካ አህጉር ልማት ያላትን ቁርጠኝነት አድንቀው ፥ በቻይና አፍሪካ የትብብር ማዕቀፍ የቀረቡትን የኢትዮጵያ ፕሮጀክቶች ይሁንታ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

አቶ ደመቀ የኢትዮጵያን ሰላም ለማረጋገጥ መንግስት የወሰዳቸው አበረታች ውሳኔዎች እና ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ያላትን የድንበር ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያላትን ቁርጠኝነት በተመለከተም ገለጻ አድርገዋል።

ልዩ መልዕክተኛ ሚስተር ዙ ቢንግ በበኩላቸው ፥ በአፍሪካ ቀንድ የሰላማዊ ልማት ኢኒሼቲቭ ስለተባለው የቻይና መንግስት ምክር ቤት አባል ዋንግ ዪ አፍሪካን በጎበኙበት ወቅት ስለተነሳው ሀሳብ ተናግረዋል።

ቻይና በአፍሪካ ቀንድ ብሎም በመላው አፍሪካ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን፣ ልማትና ብልጽግና እንዲረጋገጥ የምታበረክተውን ገንቢ ሚና አጠናክራ እንደምትቀጥል ተመላክቷል፡፡

በክልሉ ያለውን የባቡርና የወደብ ልማት ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት፣ የቻይና አንድ መንገድ አንድ ቀለበት ዕቅድ ቁርጠኝነት፣ በልማት ክልላዊ መነቃቃትን ለማፋጠን የቻይና አፍሪካ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነቶችን ጠቅሰዋል።

ቻይና የአፍሪካ ቀንድ ሀገራትን የፀጥታ፣ የልማት እና የአስተዳደር ፈተናዎችን ለመፍታት እና የአንድነት እና ራስን የማሻሻል ጎዳና እንዲከተሉ መደገፍ ትፈልጋለች ብለዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ የቀጣናው መልሕቅ ሀገር እነደመሆኗ መጠን ሰላምን በማስፈን ረገድ ገንቢ ሚና እንዳላት ልዩ መልዕክተኛው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ እና ቻይና ግንኙነታቸውን ወደ አጠቃላይ ስትራቴጂካዊ የትብብር አጋርነት እ.ኤ.አ በግንቦት 2017 ከፍ ማድረጋቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version