አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ገዢው ፓርቲ ብልጽግና በአንደኛ ጉባኤው ያስቀመጣቸውን ነጥቦች በተጨባጭ ስራ ላይ እንዲውሉ ልዩ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ የፖለቲካ ፓርቲ የስራ ሃላፊዎች ተናገሩ፡፡
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የእናት ፓርቲ ከፍተኛ የስራ ሃላፊ አቶ ያየህ አስማረ እና የኢትዮጵያ ነጻነት ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ግዛቸው አበራ፥ የሰላም እና ደህንነት፣ የኑሮ ውድነት ፣ ስር የሰደደ ሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በብቁ የአመራር ጥበብ እና ትብብር በአፋጣኝ መፍትሄ ሊቀመጥላቸው እንደሚገባ ተናግረዋል ፡፡
መሪው ፓርቲ በተለያዩ የመንግስት መዋቅር ስር እንዲፈጸሙ ግብ ያደረጋቸው አንኳር ጉዳዮች እስከ ታችኛው የቀበሌ መዋቅር ድረስ ወርደው ይፈጸሙ ዘንድ ጠንካራ የክትትል አሰራር ሊዘረጋ ይገባልም ብለዋል ፖለቲከኞቹ ፡፡
ለፓርቲ እና መንግስት አሰራር ገደብ በማበጀት ብቁ ዜጎች ወደ ፊት መጥተው የመፍትሄ አካል እንዲሆኑ ከመሪው ፓርቲ ጠንካራ ስራዎች እንደሚጠበቁም ነው የተናገሩት።
ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሃገርን በማቅናቱ የጋራ ሃላፊነት ላይ ስህተቶችን በማረም እና መልካም ጅምሮችን በማበረታታት ሂደት የራሳቸውን ሃገራዊ ጡብ ማሳረፍ ተገቢ እንደሆነም ፖለቲከኞቹ አስረድተዋል፡፡
ከፖለቲካ ፓርቲዎች ባሻገርም ሌሎች ባለድርሻ አካላት እና ህዝቡ ለጠንካራ ሃገረ መንግስት ግንባታ ሂደቱ የበኩላቸውን ሃገራዊ ሃላፊነት መወጣት እንዳለባቸውም አብራርተዋል፡፡
በአወል አበራ