Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ሩስያ በፖላንድ ድንበር አካባቢ የሚገኘውን የዩክሬን ጦር ሰፈር በአየር መደብደቧ ተሰማ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩስያ በአየር የምታረገውን ጥቃት በማስፋት በፖላንድ ድንበር አካባቢ የሚገኘውን የዩክሬን ጦር ሰፈር በተደረጋጋሚ መደብደቧን የአካባቢው ባለስልጣናትና የዓይን መስክሮች መናገራቸው ተሰማ።

የዩክሬን ምዕራባዊ ግዛት የሆነችው የልቪቭ ክልል ዋና አስተዳዳሪን ጠቅሰው አናዶሉ ዜና አገልግሎትና አልጀዚራ እንደዘገቡት ፥ በጥቃቱ 35 ሰዎች ሲሞቱ፥ በ134 ሌሎች ሰዎች ላይ የመቁሰል አደጋ ደርሷል።

የዩክሬን ባለስልጣናት በሰጡት መግለጫ፥ የሩስያ ሠራዊት በዩክሬን ምዕራባዊ ጫፍ በምትገኘውና ከፖላንድ ጋር በምትዋሰነው ልቪቭ ክልል የሚገኙ ወታደራዊ ተቋማትና ወታደራዊ ማሰልጠኛ ማዕከል ላይ ያካሄዱት ተከታታይ የአየር ጥቃት ሰፊና በዓይነቱ የተለየ ነው ብለዋል።

ሩስያ ያካሄደችው የአየር ጥቃት በዓለም አቀፍ የሰላም ጥበቃና ደህንነት ማዕከል ላይ ያነጣጠረ መሆኑንና 8 ሚሳይሎች መተኮሷንም ነው የልቪቭ ክልላዊ አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ ማክሲም ኮዚትስኪና ሌሎች የአገሪቱ ባለስልጣናት የተናገሩት።

በአንፃሩ ዩክሬን በካርኪቭ ክልል ዘመናዊ የጦር መሳሪዎችን ይዘው የሚንቀሳቀሱ የሩስያን ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ደምስሻለሁ ስትል አስታውቃለች ።

የቼክ ሪፐብሊክ የመከላከያ ሚኒስትር ጃና ሴርኖቾቫ ደግሞ ዛሬ በአገራቸው ቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ ፥ አገራቸው 725 ሚሊየን የቼክ ገንዘብ የሚያወጣ የጦር መሳሪያ ለዩክሬን መለገሳቸውን ገልጸው፥ ይህንኑ መጠን የሚያክል ወታደራዊ ድጋፍ ለመስጠት አገራቸው ዕቅድ እንዳላትም ነው ሚኒስትሯ የተናገሩት።

በሌላ በኩል ፕሬዚዳንት ፑቲን የውጭ ዜጎችን ጨምሮ በጎ ፈቃደኞች ሁሉ በጦርነቱ እንዲሳተፉ ጠቁመዋል። ይህን ተከትሎም ከ16 ሺህ በላይ የሶሪያ ወታደሮች ከሩስያ ጎነ ተሰልፈው ለመዋጋት ዝግጁ መሆናቸው ነው እየተገለጸ ያለው።

የሩስያና ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ በተነፃፃሪነት ሰላማዊ ወደ ነበረችው የልቪቭ ግዛት ነው አያሌ ዩክሬናውያን የሚሰደዱት።

የልቪቭ ከተማ ጦርነቱን ሸሽተው የሚሰደዱ ሰዎች፥ የአውሮፓ ህብረት አካል ወደሆነችው ፖላንድ የሚሸጋገሩባት ቁልፍ ከተማም ናት።

በሌላ በኩል ደግሞ ዩክሬን ውስጥ ዛሬ በመኪና ላይ በተሰነዘረ ጥቃት አንድ አሜሪካዊ ጋዜጠኛ ሲገደል፥ አንድ ሌላ አሜሪካዊ ጋዜጠኛ የቆሰለ መሆኑም ተነግሯል።

ሁለት አሜሪካውያን ጋዜጠኞች እና አንድ ዩክሬናዊ በመኪና ውስጥ ሆነው ኢርፒን በተባለች የኪየቭ ከተማ ዳርቻ ሰሜናዊ ምዕራብ ግንባር በኩል ሲንቀሳቀሱ ጥቃት እንደደረሰባቸው የኪየቭ ክፍለ ሀገር ፖሊስ ዋና አዛዥና የአገር ውስጥ ሚኒስቴር መግለጻቸውን ኤ ኤፍ ፒ ከስፍራው ዘግቧል ።

በጥቃቱ ህይወቱ ያለፈው አሜሪካዊ የፊልም ተዋናይና ጋዜጠኛ በሬንት ሬኖ መሆኑም ተጠቅሷል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version