Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በሶማሌ እና ኦሮሚያ ክልሎች ከ1 ሚሊየን በላይ የእንስሳት ክትባት ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሶማሌ እና ኦሮሚያ ክልሎች በድርቅ ጉዳት ለደረሰባቸው አካባቢዎች የእንስሳትን የበሽታ የመከላከል አቅምን ለማጎልበት የሚችል ክትባት መሰጠቱ ተገለፀ፡፡

ክትባቱ በአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢ ከ1 ሚሊየን በላይ ለሆኑ እንስሳት ነው የተሰጠው፡፡

የአርብቶ አደሩ የእንስሳት ጤና ከመጠበቅና ምርታማነት ከማሳደግ ብሎም በግጭት ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው አርብቶ አደር እና ከፊል አርብቶ አደር ለመደገፍ ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸው የግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክተር ዶክተር ውብሸት ዘውዴ ገልፀዋል፡፡

የአርብቶ አደሩ ኑሮ በእንስሳት ላይ የተመሰረተ እንደመሆኑ ከክልሎች እና የግል ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች በጋራ እና በተናጠል ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል፡፡

እንስሳቱ የበሽታ ተጋላጭነት ለመከላከልና ለመቀነስ ድጋፍ የተደረገ ሲሆን ፥ በቀጣይም 5 ሚሊየን በግዢ ሂደት ላይ መሆኑ አንስተዋል፡፡
ከዚህ ባሻገር እንደቀይ መስቀል ያሉ መንግስታዊ ያልሆኑ ዓለም አቀፍ ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች ከክልሎች ጋር በመቀናጀት የተደረገ ድጋፍ መሆኑ ዳይሬክተሩ አንስተዋል፡፡

በየዓመቱ ላለፉት አምስት ዓመታት ቀይ መስቀል የእንስሳት በሽታ የመከላከል አቅም ለማሳደግ ግመልን ጨምሮ ለቀንድና ጋማ ከብቶች ክትባት መስጠቱን የቀይ መስቀል ዓለም አቀፍ ኮሚቴ የኢኮኖሚ ደህንነት ባለሙያ ዶክተር አብዲሰላም መሐመድ ገልፀዋል፡፡

በቀጣይም ቀይ መስቀል በኢትዮጵያ በግጭት ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው አርብቶ አደር እና ከፊል አርብቶ አደር ማህበረሰቦች የእንስሳት ክትባት እና የእንስሳት ጤና አገልግሎት ይሰጣል ብለዋል።

እ.አ.አ ከጥር እስከ መጋቢት 2022 መጨረሻ ድረስ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ እንስሳት በግጭት በተጎዱ የሶማሌ እና የኦሮሚያ ክልሎች አርብቶ አደር እና ከፊል አርብቶ አደር ማህበረሰቦች በተለይም ቁቢ፣ ላጋሂዳ፣ ኩምቢ እና መዩሙሉኬ የተባሉ ወረዳዎች ክትባት ያገኛሉ ብለዋል ባለሙያው፡፡

“በሽታዎቹ የሚታወቁት ከሶማሌና ከኦሮሚያ ክልል እንስሳትና አርብቶ አደር ልማት ቢሮዎች ጋር በመተባበር በተደረገ የቅድመ ግምገማ ነው” ሲሉም አክለዋል።

በሶማሌ ክልል የቁቢ ወረዳ እንስሳት እርባታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ካሚል አህመድ በበኩላቸው ፥ በዘመቻው በህብረተሰቡ ዘንድ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን ማስገኘቱን አንስተዋል፡፡

ከእነዚህም መካከል የእንስሳት ክትባትን በቀላሉ ማግኘት፣ የእንስሳት ጤና መሻሻል እና አርብቶ አደሮች ለመከተብ በሄዱበት ወቅት ይደርስ የነበረውን የጸጥታ ስጋት ቀንሷል ነው ያሉት።

“ከግጭቱ በኋላ የሚገጥሙትን ተግዳሮቶች ከግምት ውስጥ በማስገባት ክትባቱም ሆነ ሌሎች አገልግሎቶች ባይሰጡ የእንስሳት ህልውና ላይ ጥያቄ ሊፈጥር ይችላል” ሲሉ የቁቢ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አቶ ሲያድ መሃሙድ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ግጭት እና ሁከት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ለማስቀጠል የእንስሳት ክትባት፣ የእንስሳት ጤና አያያዝ እና የማህበረሰብ አቀፍ የእንስሳት ጤና ባለሙያዎች ስልጠናን ያካተተ መርሃ ግብር በመተግበር ላይ መሆኑ ከማህበሩ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version