Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ብልጽግና ፓርቲ እውነተኛ ህብረ ብሔራዊነት በተግባር ያረጋገጠና ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሃገሩ ላይ እንዲወስን እድል ፈጥሯል- አቶ ኦርዲን በድሪ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ብልጽግና ፓርቲ እውነተኛ ህብረ ብሔራዊነት በተግባር ያረጋገጠና ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሀገሩ ላይ እንዲወስን እድል ፈጥሯል ሲሉ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለጹ፡፡
 
ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን የብልፅግና ፓርቲ አንደኛ ጉባኤን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት÷ ፓርቲው በሃገሪቱ እውነተኛ ህብረ ብሔራዊነትን በተግባር በማረጋገጥ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሃገሩ ላይ እንዲወስን እድል ፈጥሯል።
 
ቀደም ሲል በህውሓት መራሹ የኢህአዴግ አደረጃጀት ውስጥ ወጥ የሆነ አመለካከት፣ አስተሳሰብና ተግባር ያለመኖር ብልፅግና እንዲመሰረት ዋነኛ መነሻ መሆኑንም አንስተዋል።
 
በተለይም አጋር ተብለው በተፈረጁ እና ብዝሓነት ያለባቸው አካባቢዎችን ያገለለ መሆኑ እና በሃገሪቱ ወጥ የሆነ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ መፍጠር አለመቻሉ ሌላው የብልፅግና መመስረት ምክንያት መሆኑንም ጠቅሰዋል።
 
የብልፅግና ፓርቲ መመስረትም ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሃገሪቱ መፃኢ እድል ላይ የመወሰንና የመሳተፍ እንዲሁም ሃገሪቷን የመምራት እድል አጎናፅፏል ነው ያሉት።
 
እውነተኛ ህብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲጠናከር እና የጋራ እሴትና ኢትዮጵያዊ አንድነት እንዲጎለብት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም አብራርተዋል፡፡
 
ተፎካካሪ ፓርቲዎች በተለያዩ የስልጣን ደረጃ እንዲሳተፉ መደረጉ እና በህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ላይ የነበሩ ችግሮችን በመቅረፍ ሃይል እንዲያመነጭ ማስቻሉ ከብልፅግና ፓርቲ መመስረት በኋላም የተገኙ ስኬቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
 
በአንጻሩ በአሸባሪ ቡድኖች አማካኝነት የተፈጠሩ የፀጥታ ችግሮች በዜጎች ላይ ሞትና መፈናቀል መፈፀሙ በለውጥ ሂደቱ በዋናነት ያጋጠሙ ችግሮች ናቸው ብለዋል።
 
ባለፉት ዓመታት ያጋጠሙ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች፤ የኢኮኖሚ አሻጥር እንዲሁም የውጭ ጣልቃገብነት በብልፅና ፓርቲ ዘመን ያጋጠሙ ሌሎች ችግሮች መሆናቸውን አስታውሰዋል።
 
በቀጣይም የስራ እድል ፈጠራ፣ የህዝቡን ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ማቃለል እንዲሁም ሌብነትን ያለምህረት መዋጋት፤ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መቅረፍ፣ ፅንፈኝነት ማጥራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
 
በጉባኤውም ሰላምን ከማረጋገጥና ዴሞክራሲን ከማፅናት አንፃር እና የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሊፈቱ በሚችሉ እና የህዝቦች አብሮነት ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች እንደሚቀመጡ ይጠበቃል ብለዋል።
 
ፓርቲው የሃገሪቱን ብልፅግና ለማረጋገጥ በሚያከናውናቸው ተግባራትም ህዝቡ ተሳትፎውን እንዲያጎለብትም ርዕሰ መስተዳድሩ መጠየቃቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
Exit mobile version