Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የተሻለ የኦፕሬሽን አፈፃፀም እንዲኖረው እገዛ እናደርጋለን- የተባበሩት መንግስታት የአደገኛ መድሃኒቶችና ወንጀሎች ቁጥጥር ጽ/ቤት

አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የተደራጁ ድንበር ዘለል ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የተሻለ የኦፕሬሽን አፈፃፀም እንዲኖረው እገዛ እንደሚያደርግ የተባበሩት መንግስታት የአደገኛ መድሃኒቶች እና ወንጀሎች ቁጥጥር ጽ/ቤት የምስራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር ናይል ወልሽ ተናገሩ፡፡
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የተባበሩት መንግስታት የአደገኛ መድሃኒቶች እና ወንጀሎች ቁጥጥር ጽ/ቤት (unodc) የምስራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር ናይል ወልሽ ከተመራው ልዑክ ጋር ተወያዩ፡፡
በውይይታቸውም÷ አህጉራዊና ሀገራዊ ጉዳዮች በተለይም የተደራጁ ድንበር ዘለል ወንጀሎች አደንዛዥ እፅን፣ ሽብርተኝነትን፣ ህገ-ወጥ የሰዎች፣ የጦር መሳሪያና የገንዘብ ዝውውርን በጋራ ለመከላከል በሚያስችሉ ስትራቴጂክ ጉዳዮች ላይ አብሮ ለመስራት ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡
ኮሚሽነር ጄነራል በተቋሙ እየተካሄደ ስላለው ሪፎርም ባደረጉት ገለጻ÷ በወንጀል ምርመራ ተቋሙ ከዚህ በፊት ከነበረበት ሰብአዊ መብት አያያዝ ችግር ተላቆ የተሻለ ውጤት ማስመዝገቡንና የወንጀል ምርመራው ተግባር በቴክኖሎጂ የታገዘና የተጠርጣሪውን መብት በማይጥስ መልኩ በግልፅ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በቀጣይ አስር አመታት ውስጥ ተቋሙ በአፍሪካ ምርጥ አምስት የፖሊስ ተቋማት ተርታ ለማስመደብ እየሰራ መሆኑን ገልጸው÷ ይህንንም ለማሳካት የተባበሩት መንግስታት የአደገኛ መድሃኒቶች እና ወንጀሎች ጽ/ቤት ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል፡፡
ኮሚሽነር ጄነራል የተደራጁ ድንበር ዘለል ወንጀሎችና ሽብርተኝነት ለቀጠናው ስጋት መሆናቸውን ጠቁመው÷ አልሸባብንና ሌሎች አሸባሪ ቡድኖችንም በጋራ መከላከል አለብን ብለዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የአደገኛ መድሃኒቶች እና ወንጀሎች ቁጥጥር ጽ/ቤት የምስራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር ናይል ወልሽ በበኩላቸው÷ በድንበር ዘለል ወንጀሎችና በተደራጁ ወንጀሎች ዙሪያ ከተቋሙ ጋር በርካታ የተሰሩ ስራዎች እንዳሉ አስታውሰው÷ ለኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ፣ ለወንጀል መከላከልና ለወንጀል ምርመራ ቢሮ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version