አዲስ አበባ፣ የካቲት 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ዓመታት በአገራችን የሴቶች እኩልነት፣ የመብታቸው መከበር፣ የንቃተ ሕሊና ማሳደግ፣ ለኃላፊነት መብቃትን በተመለከተ የማይናቅ ዕድገት ተመዝግቧል ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ፡፡
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ዓለም ዓቀፉን የሴቶች ቀን (ማርች ኤይት) በተመለከት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የመልዕክቱ ሙሉቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
ለዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ኘሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ያስተላለፉት መልዕክት
የካቲት 29 ቀን 2014 ዓ.ም.
እንኳን ለዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በደህና አደረሰን!
ይህ ቀን በየዓመቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተዘጋጀ መሪ ቃል እንደየአገሩ ሁኔታ በመላው ዓለም ይከበራል፡፡
ባለፉት ዓመታት በአገራችን የሴቶች እኩልነት፣ የመብታቸው መከበር፣ የንቃተ ሕሊና ማሳደግ፣ ለሃላፊነት መብቃትን … ወዘተ በተመለከተ የማይናቅ ዕድገት ተመዝግቧል፡፡ የሴቶች ምኞት ገደብ ሊኖረው እንደማይችል አሳይቷል፡፡ የተሻለ ተስፋ እንዲኖራቸው ረድቷል፡፡ በርትተን የምንቀጥልበት ነው፡፡
በአንጻሩ ደግሞ ባለፉት 15 ወራት የተካሄደው ጦርነት፣ በተከታታይ የተከሰቱት የተፈጥሮ አደጋዎች ሰቆቃ ተቀባይ የሆኑት፣ ልጆቻቸውን ይዘው የተሻለ ደህንነት፣ የሚበሉት የሚጠጡትን ለማግኘት የተሰደዱት፣ የተፈናቀሉት፣ የተደፈሩት …. ሴቶች ናቸው፡፡
በመቀሌ መጠለያ ጣቢያ ያገኘኋት “ጠላ እየሸጥኩ ያሳደኳቸውን ሁለት ወንድ ልጆቼን አጣሁ”ያለችኝ፣ በደሴ የተጠለለችው የደረሰች ነፍሰ ጡር፣ በርካታ ኪሎ ሜትር ተጉዛ “ልጆቼን ምን ላድርጋቸው?” ያለችኝ እናት፣ በተለያዩ ቦታዎች የተደፈሩ ሴቶች የደረሰባቸው ቃላት የማይገልጹት ሰቆቃ፣ በሆስፒታል በመታከም ላይ የሚገኙት፣ በሱማሌ ክልል ድርቅን ለመቋቋም የተፈናቀሉት ሴቶችና ልጆች፣ በአፋር ክልል በጦርነት የተጎዱ ሕጻናት፣ ቤተሰባቸውን ትተው እያስታመሙ ያሉ እናቶች፣ ደሴ ላይ ያገኘኋትና በበጎ ፈቃደኝነት ለተፈናቃዮች በየቀኑ ቁርስ ስታቀርብ የነበረች እህት፣ ወዘተ …. ዘርዝሬ የማልጨርሰው ነገር ግን ብዙ መከራ ያሳለፉ፣ እያሳለፉ ያሉ እንዲሁም ድጋፍ እየሰጡ ያሉ ሴቶችን በዚህ ቀን በጣም አስባቸዋለሁ፡፡
በሌላ በኩል ገና በለጋ ዕድሜያቸው ከፍተኛ ጀብዱ የፈጸሙ ሴት የመከላከያ ሠራዊት አባላትን በዛሬው ዕለት አግኝቻለሁ፡፡ በጣም ያኮራሉ፡፡
ከዚህ ሁሉ በመነሳት ነው ለእኛ ኢትዮጵያውያን ይህ ቀን የተለመደው ዓይነት ቀን ሊሆን አይገባም የምለው፡፡ በስብሰባ አዳራሽ፣ በመፈክር ፣ በንግግር ብቻ የሚፈታ ጉዳይ ስላልሆነ፡፡ ቆራጥ ተግባርን ስለሚጠይቅ፡፡
ታሪካዊው የቤጂንግ ጉባኤ የሴቶች ትግል ለሰብዓዊ መብት የሚደረግ ትግል አካል መሆኑን ካረጋገጠም በኋላ በ27 ዓመታት የተከናወነውን ስንመለከት ገና ብዙ እንደሚቀረን፣ ጊዜ እየፈጀ መሆኑን እናያለን፡፡ ሆኖም ወደ ኋላ የምናፈገፍግበት ጊዜ አይደለም፡፡ የምናባክነው ጊዜ የለም፡፡
ሁላችንም ሴትም ሆነ ወንድ ተባብረን ትግሉን ከግብ ማድረስ ይጠበቅብናል፡፡ ለሴቶች በሴቶች ብቻ የሚደረግ ትግል የለም፡፡ ትግሉ የመላው ሕብረተሰብ ነው፡፡ ሃይላችንን ፣ እውቀታችንን ማሰባሰብ አለብን፡፡ በሴቶች ጉዳይ የሚሠሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የሲቪል ማህበራት፣ ተቀናጅቶ መሥራትን መለማመድ ይኖርባቸዋል፡፡
ሴቶች የጥቃት፣ የመደፈር ኢላማ መሆን ጨርሶ የለባቸውም፡፡ ከመፈክር ባለፈ ከሥር መሠረቱ እንሥራበት፡፡
በቀጣይ የተፈናቀሉትን ወደ ቦታቸው መመለስ፣ ማቋቋም፣ ወላጅ ያጡ ሕጻናትን መሰብሰብ፣ ሥነ ልቦናዊ ድጋፍ መስጠት ፣ የፈረሰውን መገንባት… ይጠብቀናልና ከምን ጊዜውም በላይ መተባበር አለብን፡፡ ወደ ቦታቸው ብንመልሳቸው እንኳን ጥሪት የሌላቸውን ካልደገፍን ውጤት አልባ ይሆናል፡፡
በርካታ የቤት ሥራዎች አሉብን፡፡ በርካታ መሰናክሎችን ያለፍን ሴቶች ጫካውን የምንጋርድ ዛፍ መሆን ስለሌለብን ከሁላችንም ብዙ ይጠበቃል፡፡ ለዚህ ነው ለብዙ ሴቶች፣ ለእኛም ኢትዮጵያውያን የሴቶች ቀን የአንድ ቀን ጉዳይ፣ የአንድ ወር ጉዳይ ሳይሆን በዓመት የ365 ቀን ጉዳይ ነው ፣የዕለት ተዕለት ሥራ ነው የምለው፡፡
– ከተባበርን እንችላለን፡፡
– ለተግባር እንነሳ፡፡