Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኢትዮጵያና የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች የ100 ሚሊየን ዶላር የብድር ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 16፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያና የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች የ100 ሚሊየን ዶላር የብድር ስምምነት ተፈራረሙ።

የብድር ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ እና የከሊፋ ፈንድ የልማት ድርጅት ሊቀ መንበር ሁሴን ጃሲን አልኖዊስ ተፈራርመውታል።

ብድሩም በረጅም ጊዜ የሚከፈልና ቀላል የብድር አይነት መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ ተናግረዋል።

በዋናነት በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ሃገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለማገዝ ያለመና፥ ለአነስተኛ መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት እንደሚውልም አስረድተዋል።

በተጨማሪም ለወጣቶች እና ሴቶች የስራ ዕድል ፈጠራ፣ ጀማሪ ስራ ፈጣሪዎችን ለማበረታታት፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለመደገፍ እንዲሁም ለአቅም ግንባታ ይውላልም ነው ያሉት።

ብድሩ ሃገራቱ የሚያደርጉት ትብብር ማሳያ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥ የኢኮኖሚ እድገትን ለማጠናከር የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የከሊፋ ፈንድ የልማት ድርጅት ሊቀ መንበር ሁሴን ጃሲን አልኖዊስ በበኩላቸው የብድር ስምምነቱ የየሃገራቱ መሪዎች የደረሱት ስምምነት አካል መሆኑን ገልጸዋል።

አያይዘውም ፈንዱ በቀጣይም ከኢትዮጵያ ጋር የሚያደርገውን ትብብር አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

Exit mobile version