አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሊያ የጸጥታ ሃይል የአገሪቷን ሰላም የማስከበር ሃላፊነት በሁለት ዓመት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ከሶማሊያ የአፍሪካ ሕብረት ሰላም አስከባሪ ተልዕኮ (አሚሶም) ሊረከብ መሆኑ ተገለጸ።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በፈረንጆቹ 2007 ባስተላለፈው ውሳኔ መሰረት አሚሶም ሶማሊያን ከአልሸባብ ነጻ ለማድረግ እና በሀገሪቱ ሰላም የማረጋጋት ተልዕኮ ወስዶ መሰማራቱ ይታወቃል።
የአፍሪካ ሕብረት የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት ባዘጋጀው የጊዜና የግዳጅ አፈጻጸም ማዕቀፍ አማካኝነት የሶማሊያ የጸጥታ ሃይል የአገሪቷን ጸጥታ የማስጠበቅ ሙሉ ሃላፊነት በሁለት ዓመት ውስጥ ከአሚሶም እንደሚረከብ ኢዜአ ዘግቧል።
የአፍሪካ ሕብረት ሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ስያሜ ወደ ሶማሊያ የአፍሪካ የሽግግር ተልዕኮ እንደሚቀየርም ነው የተገለጸው።
ተልዕኮው የሶማሊያ ምድርና አየር ሃይሎች እንዲሁም የስለላና ደህንነት ተቋማትን አቅም መልሶ በመገንባት በሁለት ዓመት ውስጥ ሙሉ ሃላፊነታቸውን እንዲወስዱ የማዘጋጀት ስራ ያከናውናል ተብሏል።
በሽግግሩ ዙሪያ የአፍሪካ ሕብረትና የሶማሊያ መንግስት ከመግባባት ላይ መድረሳቸው የተገለጸ ሲሆን፥ የአፍሪካ ሕብረት የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት በያዝነው ወር ላይ ማዕቀፉን ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።
ምክር ቤቱ ማዕቀፉን አሚሶም ግዳጁን ከሚያጠናቅቅበት የፈረንጆቹ መጋቢት 31 ቀን 2022 በፊት ለጸጥታው ምክር ቤት አቅርቦ እንደሚያጸድቅ የዘ ኢስት አፍሪካ ዘገባ ያመለክታል።
ከ15 ዓመት በላይ የቆየው በሶማሊያ የአፍሪካ ሕብረት ሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ከኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ብሩንዲና ጅቡቲ የተውጣጡ 20 ሺህ የሚጠጉ ወታደሮችን የያዘ ሃይል ነው።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!