Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በገበያ መር ክላስተር ግብርና አርሶ አደሮች ከዕለታዊ ፍጆታ ባለፈ እስከ 50 በመቶ ምርታቸውን ለገበያ አቅርበዋል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት 2 ዓመታት በገበያ መር የክላስተር ግብርና የተሳተፉ አርሶ አደሮች ከዕለታዊ ፍጆታ ባለፈ ከ20 እስከ 50 በመቶ ምርታቸውን ለገበያ ማቅረባቸውን የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ገለጸ።
 
በኤጀንሲው የግብርና ኮሜርሻላይዜሽን ዘርፍ ዳይሬክተር ተጫነ አዱኛ÷አርሶአደሮች ከግለሰብ ፍጆታ ባለፈ ገበያ መር የሆነ ምርት እንዲያቀርቡ የሚያስችል ፕሮጀክት ተነድፎ ምርቶችን በመምረጥና አካባቢዎችን በማደራጀት ወደ ስራ ተገብቷል ብለዋል።
 
ፕሮጀክቱ እ.አ.አ ከ2019 እስከ 2024 የሚቆይ መሆኑንና የግብርና ኮሜርሻላይዜሽን ወይንም ገበያ መር የክላስተር ግብርና እንደሚባል የገለጹት ሃላፊው÷ በኢትዮጵያ የተለያዮ አካባቢዎች እየተተገበረ ይገኛል ሲሉ አብራርተዋል።
 
ተፈላጊ የሆኑ እንደ ስንዴ፣ በቆሎ፣ የቢራ ገብስ፣ ሰሊጥ፣ ጤፍ፣ አቦካዶ፣ ማንጎ፣ ሙዝ፣ ሽንኩርትና ቲማቲም ምርቶችን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል በሚገኙ 300 ወረዳዎችና በአርሶ አደር የክላስተር ቡድኖች አማካኝነት ወደ ህብረተሰቡ ቀርበዋል ነው ያሉት።
 
በተዋቀሩት የክላስተር ቡድኖች 3 ነጥብ 6 ሚሊየን አርሶ አደሮች እንደተሳተፉ ሃላፊው መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
 
ከነዚህም ውስጥ 1 ነጥብ 9 ሚሊየን አርሶ አደሮች በምርት ክላስተር ቡድን ራሳቸውን በማደራጀት በየዓመቱ ከሚሰበስበው የግብርና ምርት በተሻለና ከእለታዊ ፍጆታ ባለፈ ከ20 እስከ 50 በመቶ ምርት ለገበያ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።
 
ፕሮጀክቱ የግብዓት አቅርቦት፣ የምርት ስራ፣ ክምችትና የገበያ ሰንሰለትን ማቀፉን ጠቁመው አርሶአደሮች ምርት የት እሻጣለሁ አንዳይሉ ከገዢው ጋር በኮንትራት ስምምነት የግብይት ትስስር የሚፈጥሩበት አሰራር መዘርጋቱን አስታውቀዋል።
 
በቀጣይም በሌሎች አካባቢዎች በከብትና ዶሮ እርባታ፣ በአሳና ወተት ምርት እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ገበያ መር የክላስተር ግብርና ስራዎች እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል።
 
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version