Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በመጪው የዒድ-አል አድሃ አረፋ በዓል በርካታ ሰዎችን የሚያሳትፍ ታላቅ ኮንቬንሽን ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ እናዘጋጃለን – በድር ኢትዮጵያ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) መጪውን የረመዳን ኢድ ስግደት ምክንያት በማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለሙስሊሙ የዳያስፖራ አባላት ወደ ሀገር ቤት እንዲገቡ ያቀረቡትን ጥሪ በደስታ እንደሚቀበለው “በድር ኢትዮጵያ ዓለም ዓቀፍ የሙስሊሞች ድርጅት” አስታወቀ፡፡

የ”በድር ኢትዮጵያ ኮንቬንሽን” ላለፉት 21 ዓመታት ከኢትዮጵያ ውጭ ሲዘጋጅ እንደነበረ የድርጅቱ ቃል አቀባይ ብርሃን አሕመድ የተናገሩ ሲሆን 22ኛውን የድርጅቱ ዓመታዊ ጉባዔ በኢድ-አል አድሃ አረፋ በዓል ለመጀመሪያ ጊዜ በርካታ ዳያስፖራዎችን ወደ አዲስ አበባ በማስገባት በኢትዮጵያ ለማዘጋጀት ማሰቡን ጠቁመዋል፡፡

በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች መጪውን የዒድ በዓል በሀገራቸው እንዲያከብሩም ሠፊ ሥራዎች እየሠራ መሆኑን ድርጅቱ ገልጿል፡፡

ድርጅቱ ሁሉን አቀፍና ተባብሮ መሥራት የሚችል ድርጅት መሆኑን ከ”አባይ ንጉሶች” እና በዋሽንግተን ዲሲ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በጋራ በመሆን ለኅዳሴው ግድብ ግንባታ በአጭር ጊዜ ውስጥ 1 ሚሊየን 50 ሺህ የአሜሪካ ዶላር በማሰባሰብ ማሳየቱን የድርጅቱ ፕሬዚዳንት አሕመድ ወርቁ አስታውሰዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ፥ ከጦርነት ጋር በተያያዘ ትምህርት ቤቶችንና የጤና ተቋማትን ጨምሮ የማኅበረሰብ መሠረተ-ልማቶች መጎዳታቸውን አንስተው በመልሶ ግንባታው የየድርሻቸውን እንደሚወጡ ነው ያስታወቁት፡፡

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ በበኩላቸው፥ “በድር ኢትዮጵያ” ሀገራዊ ጥሪውን ተከትሎ መጪውን የኢድ በዓል በኢትዮጵያ ለማክበር በመዘጋጀታቸው ምሥጋና ያቀረቡ ሲሆን በሂደቱ ኤምባሲው አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርግም ቃል መግባታቸውን ከኤምባሲው ያገኘነው መረጃ አመልክቷል፡፡

“በድር ኢትዮጵያ” አሜሪካ ካናዳ እና አውሮፓን ጨምሮ 27 የሙስሊም ማኅበረሰብ አባላትን የሚወክል በፈረንጆቹ 2000 የተቋቋመ ድርጅት ነው

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version