አዲስ አበባ፣የካቲት 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር አምራቾችና ላኪዎች ማህበር እንዲሁም ሊንሰን ሮዝ አበባ ላኪ ማህበር በአሸባሪው ህወሓት ለተፈናቀሉና በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የ6 ሚሊየን ብር የገንዘብና የዓይነት ድጋፍ አደረጉ።
የ5 ሚሊየን ብር ድጋፉ÷ ከኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሠራተኞችና ከሠራተኞች ክበብ የተሰበሰበ ነው ተብሏል።
ድጋፉን የብሔራዊ አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ የተረከቡ ሲሆን÷ “በችግርና በክፉ ቀን አብሮ መሆን ኢትዮጵያዊ ባህላችን ነው” ሲሉም ሌሎች ተቋማት ተመሳሳይ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ቶሌራ በበኩላቸው፥ ድጋፉ ኢትዮጵያ የገጠማትን ሰው-ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋ በጋራ ለመቋቋም አብሮነታችንን ለማሳየት የተደረገ ነው ብለዋል።
ኢንስቲትዩቱ ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች አራት ጊዜ ድጋፍ ማድረጉንም አሚኮ ዘግቧል፡፡
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር አምራቾች እና ላኪዎች ማህበርና ሊንሰን ሮዝ አበባ ላኪ ማህበር በአሸባሪው የህወሓት ቡድን ለተፈናቀሉ በደቡብ ወሎ ዞን ለሚገኙ ወገኖች የሚውል የአንድ ሚሊየን ብር የዓይነት እና የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል።
ድጋፉን የተረከቡት የደቡብ ወሎ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ተስፉ ዳኜ ፥ በዞኑ ውስጥ የተቸገሩ ወገኖችን ለዕለት ደራሽ ችግር መፍቻ ይሆናል ብለዋል።
በአዲስና በነባር ከ29 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ የጠቀሱት የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ኢብራሂም ይመር ፥ ሁሉም የሚችለውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።