Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ለአዳዲስ ነዋሪዎች የቤት ኪራይ የምትከፍለው ከተማ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 16፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ቴኦራ የተሰኘቸው የጣሊያን ከተማ ኑሯቸውን በከተማዋ ለማድረግ ለሚመጡ አዳዲስ ነዋሪዎች የቤት ኪራይ ትከፍላለች።

በጣሊያን የሚገኙ አነስተኛ ከተሞች የዜጎችን ቀልብ በመሳብ የነዋሪዎችን ቁጥር ለመጨመር የተለየዩ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ።

ለአብነትም በቅርቡ በደቡብ ጣሊያን ሲሲሊ ደሴት ውስጥ የምትገኘው ሳምቡክ ከተማ መኖሪያ ቤት በአንድ ዶላር ዋጋ በይፋ መሸጥ መጀመሯ ይታወሳል።

ይህም በሀገሪቱ በገጠር እና ሩቅ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች ወደ ትላልቅና ዘመናዊ ከተሞች የሚያደርጉትን ፍልሰት ለመቀነስ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

ይሁን እንጅ እቅዱ ሰዎች ቤቶቹን በርካሽ ዋጋ ገዝተው የእረፍት ጊዜያቸውን እንዲያሳልፉ ከማድረግ ባለፈ ዘላቂ ኑሯቸውን በከተማዋ እንዲመሰርቱ እንደማያስችል ይነገራል።

ይህን ችግር ለመቅረፍም በሀገሪቱ ደቡብ ካምፓኒያ ግዛት የምትገኘው ቴኦራ ከተማ ለአዳዲስ ነዋሪዎች የቤት ኪራይ ክፍያ እንደምትሰጥ አስታውቃለች።

በዚህ መሰረትም ኑሯቸውን በቴኦራ ለማድረግ ወደ ከተማዋ ለሚያቀኑ አዳዲስ ነዋሪዎች ለቤት ኪራይ ክፍያ 162 የአሜሪካ ዶላር በየወሩ በነጻ የሚሰጥ ይሆናል።

ክፍያው ለሁለት ተከታታይ ዓመታት የሚቀጥል ሲሆን፥ ከሁለት ዓመት በኋላም ነዋሪው ቤቱን በ5 ሺህ ዩሮ በመግዛት የራሱ ማድረግ እንደሚችል ተገልጿል።

ምንጭ፦ ሲ ኤን ኤን

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

Exit mobile version