የሀገር ውስጥ ዜና

የአፍ መፍቻ ቀን በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ተከበረ

By Tibebu Kebede

February 24, 2020

አዲስ አበባ፣ የካቲት 16፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍ መፍቻ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ21ኛ ጊዜ በሃገራችን ደግሞ ለ10ኛ ጊዜ በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ተከበረ።

ቀኑ የትምህርት ሚኒስቴር ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዳሚ እንዲሁም ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር፥ የቋንቋ መብት፣ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እና የኢትዮጵያ አፋዊ ቋንቋዎችን ተቀቋማዊ ማድረግ በሚል መሪ ቃል ተከብሯል።

የትምህርት ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ጽዮን ተክሉ የአፍ መፍቻ ቀን መከበሩ ህዝቦች የአፍ መፍቻ ቋንቋን ጠብቀው እንዲያቆዩ ያስችላቸዋል ብለዋል።

ቋንቋዎች በትምህርት ፖሊሲ ውስጥ ተካተው ዜጎችም ትምህርታቸውን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ እየተደረገ ያለውን ጥረት እንደሚያጠናክረውም ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ባዬ ይማም በበኩላቸው፥ ቋንቋዎች የማህበረሰብ መመስረቻ፣ የማንነት መገለጫና መለያ ዋነኛ መሳሪያዎች በመሆናቸው በመጥፋት ላይ ያሉ ቋንቋዎችን ከመጥፋት ለመታደግ ሁሉም የበኩሉን አስተዋፅኦ ሊያደርግ ይገባል ነው ያሉት።

በመድረኩ ላይ በሀገሪቱ በመጥፋት ላይ ያሉ ቋንቋዎችን ከመታደግ አኳያ በተለያዩ ተቋማትና ምሁራን በኩል ልዩ ልዩ ስራዎች እየተሰሩ ነው መባሉን ከትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ! https://t.me/fanatelevision