Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኢራን በኮሮና ቫይረስ ስጋት ትምህርት ቤቶችንና ባህላዊ ማዕከሎችን ዘግታለች

አዲስ አበባ፣ የካቲት 16፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢራን የኮሮና ቫይረስ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች እና ባህላዊ ማዕከሎች እንዲዘጉ መወሰኗ ተሰምቷል።

በቻይና ሁቤይ ግዛት ውሃን ከተማ የተቀሰቀሰው የኮሮና ቫይረስ አሁን ላይ በተለያዩ የዓለም ሀገራት እየተዛመተ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።

በቅርቡ ወደ ኢራን ማርካዚ ግዛት በገባው በዚህ ቫይረስ ስምንት የሀገሪቱ ዜጎች ለህልፈት መዳረጋቸውን የሀገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ቁጥርም 43 መድረሱ ነው የተገለጸው።

ይህን ተከትሎም ሀገሪቱ ቫይረሱ በተከሰተባቸው ግዛቶች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች እና የተለያዩ ባህላዊ ማዕከሎች እንዲዘጉ መወሰኗ ተሰምቷል።

ከዚህ ባለፈም የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሃሰን ሮሃኒ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ብሄራዊ የመቆጣጠሪያ ማዕከል እንዲቋቋም ትዕዛዝ መስጠታቸው ተገልጿል።

የሚቋቋመው ማዕከልም በሀገሪቱ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የሚደረገውን ዘመቻ የሚያስተባብር ይሆናል።

በሌላ በኩል በኢራን በቫይረሱ የተጠቁ ዜጎች ቁጥር መጨመሩን ተከትሎ ቱርክ፣ አፍጋኒስታን እና ፓኪስታን ከሀገሪቱ የሚያዋስናቸውን ድንበር ዘግተዋል ተብሏል።

በአሁኑ ወቅት በቻይና ብቻ በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 2 ሺህ 592 ሲደርስ፥ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር ደግሞ ወደ 77 ሺህ 150 አሻቅቧል።

በደቡብ ከሪያ በአንድ ቀን ውስጥ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር በእጥፍ ጨምሮ 760 ሲደርስ 7 የሚሆኑ ዜጎችም ለህልፈት ተዳርገዋል።

ምንጭ፦ አልጀዚራ

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

Exit mobile version