አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰሞኑን በኢትዮጵያ ቆይታ ያደረገው የሩስያ ከፍተኛ ልዑክ አባል የሆነችው የ22 ዓመቷ ማዲና ላኮባ የአማርኛ ቋንቋን አቀላጥፋ መናገር፣ መስማት፣ ማንበብና መፃፍ ትችላለች።
እሷና ጓደኞቿ ከዩኒቨርሲቲ የቀሰሙትን የአማርኛ ቋንቋ ክህሎት እንዲያዳብሩ ከረዷቸው መንገዶች ዋነኛው የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዜናዎችን በተለያዩ አማራጮች መከታተላቸው መሆኑን ትናገራለች፡፡
የሩስያ ፌደሬሽን ምክር ቤት ሴናተር ኢጎር ሞሮዞቭ ልዩ ረዳት የሆነቸው ማዲና ላኮባ እንደምትለው እሷ፣ ጓደኞቿ እና የቤተሰቧ አባላት ስለ ኢትዮጵያም ሆነ ስለ ቀጣናው ወቅታዊ ሁኔታዎች ለመረዳት የፋናን ድረ ገጽ፣ ፌስቡክ እና ቴሌቪዥን የአማርኛ ዜናዎችን በንቃት እንደሚከታተሉ ነው ያጫወተችን፡፡
“በተለይም ኢትዮጵያ በውስጥ ችግሯ እና በውጭ ጫና የተነሳ ችግር ውስጥ በገባችበት ወቅት፤ ከመተኛቴ በፊትም ሆነ ከእንቅልፌ ከነቃሁ በኋላ የእጅ ስልኬን ከፍቼ በመጀመሪያ የማየው የፋናን የፌስቡክ ገፅ ነበር” ስትል ስለ ኢትዮጵያ ያላትን ፍቅር ትገልፃለች፡፡
የፋና ዜናዎች የንባብ ስብስብ እንዳላቸው እና የሚዲያ ተቋሙ በሩሲያ የበለጠ ተደራሽ እንዲሆን የሚያስችሉ መንገዶችን እያፈላለገች መሆኗንም ነው የምትናገረው፡፡
በሩሲያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የአማርኛ ቋንቋን ማጥናት የተለመደ ነገር መሆኑን የምትናገረው ማዲና ላኮባ፥ በሞስኮ ስቴት ዩኒቨርሲቲ በእስያ እና አፍሪካ ጥናቶች የትምህርት ክፍል፥ የኢትዮጵያን ታሪክ እና ባህል ስትማር ስለ አገሪቱ ቀደም ሲል ካላት እውቀት ጋር ተዳምሮ ቋንቋውን በጥልቀት የመረዳት ጉጉት እንደፈጠረባት ታስረዳለች።
“ሚዲያ በመከታተል የአንድን አገር ቋንቋ የበለጠ ለማዳበር እንደሚቻል ባውቅም፥ በኢትዮጵያ ካሉ ሚዲያዎች በአንዱ ላይ ማተኮር እንዳለብኝ በማመን እና በተለያዩ መስፈርቶች በመታገዝ ፋናን ምርጫዬ ላደርግ ችያለሁ” ስትል ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ትገልፃለች- ወጣቷ ሩስያዊት።
በኢትዮጵያ የሩስያ አምባሳደር ኤቭጀኒ ተረኪን፥ አገራቸው ሩስያ ላለፉት ምዕት ዓመታት አገራቸው ሩስያ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማቷ የአማርኛ ቋንቋን እያስተማረች እንደምትገኝ ከዚህ ቀደም ነግረውናል፡፡ ራሳቸው አምባሳደር ተረኪንም አማርኛን አሳምረው እንደሚናገሩ ይታወቃል።
በወንደሰን አረጋኸኝ