Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ የሰዎች ለሰዎች ድርጅት በችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰዎች ለሰዎች ድርጅት በችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ጥሪ አቀረቡ፡፡

ፕሪዚዳንቷ ይህን ያሉት የሰዎች ለሰዎች ድርጅት በኢትዮጵያ ስራ የጀመረበትን 40ኛ ዓመት ባከበረበት መርሃ ግብር ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ነው፡፡

በመርሃ ግብሩም የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴና የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ የሰዎች ለሰዎች ድርጅት ባለፉት 40 ዓመታት በኢትዮጵያ ላከናወናቸው በጎ ስራዎች ምስጋና አቅርበው ፥ በተለይ በችግር ውስጥ የነበሩ ዜጎች ራሳቸውን እንዲችሉ በማድረግ ረገድ ድርጀቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቅሰዋል፡፡

ይህም ለሌሎች ድርጅቶች አርዓያ የሚሆን ተግባር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ድርጅቱ በቀጣይ በችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተደድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው የሰዎች ለሰዎች ድርጅቱ እስካሁን ባለው ሂደት በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ 3 ነጥብ 3 ሚሊየን ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረጉን አንስተው ፥ በርካታ ዜጎችን አስተምሮ ለትልቅ ደረጃ እንዳበቃ ገልጸዋል፡፡

ድርጅቱ ላበረከተው አስተዋጽኦም የእውቅና ስጦታ አበርክተዋል፡፡

የሰዎች ለሰዎች ድርጅት ከቀናት በፊት በሰጠው መግለጫ በኢትዮጵያ በጦርነቱ የተፈናቀሉና የንብረት ውድመት የደረሰባቸው ወገኖችን ለመደገፍ 2 ሚሊየን ዮሮ መድቦ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

በጀርመናዊው ካርል ሄንዝ በም የተመሰረተው የሰዎች ለሰዎች ድርጅት ባለፉት 40 ዓመታት በኢትዮጵያ ከ461 በላይ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ከ500 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተጠቃሚ ማድረጉም ከድርጅቱ የተገኘው መረጃን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version