አዲስ አበባ፣ የካቲት 15፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 15ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በተለያዩ ከተሞች ተካሂደዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ ቡና፣ ሀዋሳ ከተማ፣ ባህርዳር ከነማ እና ድሬዳዋ ከተማ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል።
ወላይታ ድቻን በአዲስ አበባ ስታዲየም ያስተናገደው ኢትዮጵያ ቡና 3 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸንፏል።
የኢትዮጵያ ቡናን የማሸነፊያ ግቦች ሃብታሙ ታደሰ እና አቡበከር ናስር ሲያስቆጥሩ፥ የወላይታ ድቻን ብቸኛ ግብ ደግሞ ባዬ ገዛኸኝ አስቆጥሯል።
ወደ ሀዋሳ በማቅናት ሀዋሳ ከተማን የገጠመው ፋሲል ከነማ ደግሞ 3 ለ 2 በሆነ ውጤት ተሸንፏል።
የዋሳ ከተማን የማሸነፊያ ግቦች ብሩክ በየ፣ ሄኖክ ድልቢ እና መስፍን ታፈሰ ሲያስቆጥሩ፥ የፋሲል ከነማን ግቦች ደግሞ ሱራፌል ዳኛቸው እና አዙካ ኢዙ አስቆጥረዋል።
ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ እና ወልቂጤ ከተማ በወልዋሎ ስታዲየም ያደረጉት ጨዋታ 3 ለ 3 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።
በተጨማሪም ባህር ዳር ከነማ ስሑል ሽረን እንዲሁም ድሬዳዋ ከተማ መቐለ 70 እንደርታን 1 ለ 0 በሆነ ተመሳሳይ ውጤት አሸንፈዋል።
ፕሪሚየር ሊጉን ቅዱስ ጊዮርጊስ በ27 ነጥብ በአንደኝነት ሲመራ ፥ፋሲል ከነማ እና መቐለ 70 እንደርታ ደግሞ በ26 እና 25 ነጥብ 2ኛ እና 3ኛ ደረጃ ላይ ጠቀምጠዋል።
የፋሲል ከነማው ሙጂብ ቃሲም 14 ግቦችን በማስቆጠር የፕሪምየር ሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሲሆን፥ የሀዋሳ ከተማው ብሩክ በየነ ደግሞ 9 ግቦችን ከመረብ በማገናኘት 2ኛ ደረጃን ይዟል።