ዓለምአቀፋዊ ዜና

በቱርክ በደረሰ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ የ8 ሰዎች ህይወት አለፈ

By Tibebu Kebede

February 23, 2020

አዲስ አበባ፣ የካቲት 15፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በምስራቅ ቱርክ ቫን ግዛት በደረሰ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ የ8 ሰዎች ህይወት አለፈ።

የሀገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሱሊማን ሶይሉ ፥በኢራን ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው ቫን ግዛት በዛሬው ዕለት የመሬት መንቀጥቀት አደጋ መከሰቱን ተናግረዋል።

በደረሰው አደጋም ከሞቱት ሰዎች በተጨማሪ 37 የሚሆኑ ዜጎች ላይ ከባድ እና ቀላል ጉዳት መድረሱን ነው የገለጹት።

በሬክተር ስኬል 5 ነጥብ 7 የተመዘገበው ይህ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ 1 ሺህ 66 በላይ ህንጻዎችን ማፈራረሱም ተመላክቷል ።

አደጋው 43 መንደሮችን እንዳዳረሰ የገለጹት ሚኒስትሩ፥ የተጨማሪ ሰዎችን ህይወት ለመታደግ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች በስፍራው መሰማራታቸውን ጠቁመዋል።

የኢራን ባለስልጣናት በበኩላቸው የአዳጋ ጊዜ ሰራተኞችን አደጋው ወደ ተከሰተባቸው አካባቢዎች መላካቸውን አስታውቀዋል።

ቱርክ እና ኢራን በተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ የሚያስተናግዱ ሀገራት መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።

በሳለፍነው ወር ብቻ በቱርክ በደረሰ ተመሳሳይ አደጋ 40 ሰዎች ለህልፈት መዳረጋቸው የሚታወስ ነው።

ምንጭ፦ አልጀዚራ