ቢዝነስ

አራት የቅመማ ቅመም ምርቶች እና ጓያ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓቱን ተቀላቀሉ

By Alemayehu Geremew

February 24, 2022

አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ድንብላል፣ አብሽ፣ ቁንዶ በርበሬና ጥቁር አዝሙድ እንዲሁም ጓያ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ የግብይት ስርዓታቸው ዛሬ በይፋ መጀመሩን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ድርጅት አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ድርጅት እንደገለጸው እነዚህ ምርቶች ሲካተቱ ምርት ገበያው የሚያገበያያቸው ምርቶች ብዛት ከ12 ወደ 17 ከፍ ያደርገዋል ተብሏል፡፡

አንድ ኩንታል ጥቁር አዝሙድ በ26 ሺህ 500 ብር፥ አንድ ኩንታል አብሽ በ12 ሺህ ብር መገበያየቱም ተጠቁሟል፡፡

በየዓመቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ348 ሺህ ቶን በላይ ቅመማ ቅመም ይመረታል ነው የተባለው፡፡

እነዚህ ቅመማ ቅመሞች በአብዛኛው በዓለም ገበያ ተፈላጊ ሲሆኑ፥ በተለይም አብሽን በማምረት ኢትዮጵያ ከፍተኛውን ድርሻ ትወስዳለች።

በየዓመቱ ወደ ውጭ የሚላከው የቅመማ ቅመም ምርት 15 ሺህ ቶን ሲሆን ፥ ከጠቅላላው ዓመታዊ ምርት መጠን ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ መሆኑ ተገልጿል።

ጓያም በየዓመቱ ከ2 ነጥብ 6 ሚሊየን ኩንታል በላይ እየተመረተ ወደ ውጭ የሚላከው ከ775 ሺህ ኩንታል ያልዘለለ መሆኑን ከምርት ገበያ ድርጅቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡