Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የአዳማ ሪፌራል ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የህክምና ዶክተሮችን አስመረቀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዳማ ሪፌራል ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የውስጥ ደዌና ከፍተኛ የቀዶ ህክምና ስፔሻልስቶችን ጨምሮ በተለያዩ ሙያዎች ያሰለጠናቸውን 140 ዶክተሮችን ዛሬ አስመረቀ።

ከተመራቂዎቹ መካከል ደቡብ ሱዳን የህክምና ስፔሻልስቶች ይገኙበታል።

በምረቃው ስነ ስርዓት የተገኙት የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ነጋሽ ስሜ እንደገለጹት በክልሉ ከተሞችና ገጠራማ አካባቢዎች ካንሰርና ስኳርን ጨምሮ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታ እየተስፋፋ መጥቷል

በክልሉ በሚገኙ የመጀመሪያና ሪፌራል ሆስፒታሎች የህክምና መሳሪያና መድኃኒትን ጨምሮ የውስጥ ዳዌና የቀዶ ህክምና ሐኪሞች እጥረት መኖሩንም ተናግረዋል።

ለዚህም የአዳማ ሪፌራል ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ግንባር ቀደም መሆኑን ጠቅሰው ኮሌጁ የሰው ህይወት ለማዳን የሚያስችል እውቅትና ክህሎት ለማስታጠቅ ተግባር ተኮር ስልጠናና ምርምር ሥራዎችን ማከናወን እንደሚገባው ጠቁመዋል።

ሰልጣኞቹ በቆይታቸው ያገኙትን እውቀት ወደ ተግባር በመተርጎም ማህበረሰቡን በማገልገል ምሳሌ መሆን አለባቸው ብለዋል።

የኮሌጁ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መኮንን ፈይሳ በማህፀን፣ በውስጥ ደዌ፣ በህፃናትና በከፍተኛ ቀዶ ህክምና እንዲሁም በጠቅላለ ሐክም ስፔሻልስቶችን እያሰለጠነ ነው።

ዛሬ ለምረቃ የበቁት 140 የህክምና ዶክተሮች አሁን በስፋት የሚስተዋለውን አጣዳፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ተናግረዋል።

በተለይ በክልሉ የመጀመሪያ፣ ስፔሻላይዝድና ሪፌራል ሆስፒታሎች የሚታዩትን የማህፀን፣በውስጥ ደዌ፣ የህፃናትና ከፍተኛ ቀዶ ህክምና ያለው የከፍተኛ ሙያተኞች እጥረት የሚፈታ ነው ብለዋል።

ሰልጣኞቹ በቆይታቸው ለህብረተሰቡ የጠቅላላ ህክምና አገልግሎት፣ መካከለኛና ከፍተኛ የቀዶ ጥገና ህክምና በመስጠት ሙያዊ ብቃታቸውን በተግባር ያስመሰከሩ በማለት አስረድተዋል።

ኮሌጁ ከ400 በላይ አልጋ ያለው፣ ማስፋፊያ ግንባታ፣ የጥናትና ምርምር ማዕከላት፣የተማሪዎች መኖሪያና መመገቢያ ህንፃዎች ከአንድ ቢሊዮን 300ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በመገንባት ለአገልግሎት ዝግጁ አድርጓል።

ምንጭ፦ ኢዜአ

Exit mobile version