Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በዘንድሮው የአካባቢ ጥበቃ ስራ 2 ሚሊየን ሄክታር መሬት ለመሸፈን እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የግብርና ሚኒስቴር እስከ የካቲት 30 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚቆየው የአካባቢ ጥበቃ ስራ 2 ሚሊየን ሄክታር መሬት ለመሸፈን እየተሰራ መሆኑን አስታወቀ።

የግብርና ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ካባ ኡርጌሳ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ከጊዜ ወደ ጊዜ የህብረተሰቡ ግንዛቤ እያደገ በመምጣቱ ባለፉት አመታት የተሰሩት ስራዎች በውጤት የታጀቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከአካባቢ ጥበቃ ጎን ለጎን በንብ ማነብ እና በእንስሳት እርባታ ላይ ስራ አጥ ወጣቶች ተሰማርተው የስራ እድል ተፈጥሮላቸዋል ብለዋል።

የኦሮሚያ ክልል እርሻ እና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ሀላፊ እንዳልካቸው ተፈሪ በበኩላቸው፥ የአፈር እና ውሃ ጥበቃ ስራዎች በአንድ ላይ በመሰብሰብና የተራቆቱ አካባቢዎችን በማልማት የእስካሁኑ የዘርፉን ተሳትፎ ውጤታማ መሆኑን ተናግረዋል።

በአርሶ አደሮች ጉልበት ብቻ የሚደረገው ይህ ጥረት አሁን ካለው የከባቢ አየር መለዋወጥ ጋር ስለማይመጣጠን በሜካናይዜሽን መደገፍ ይኖርበታል ነው ያሉት።

ከዚህ አንጻርም ባለፉት አመታት በገጠር አካባቢ ብቻ ሲሰራ የነበረውን የአካባቢ ጥበቃ ስራ የትላልቅ ከተማ ነዋሪዎችን በተለያዩ ስራዎች እንዲሳተፉ በማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አያይዘውም ሶስት ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል በ4 ሺህ 890 የችግኝ ጣቢያዎች ላይ የመንከባከብ ስራው መቀጠሉንም ነው የተናገሩት።

በአፈወርቅ አለሙ

Exit mobile version