Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

አልማ በአሜሪካ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አባቶችና ምዕመናን ጋር በመተባበር የእለት ደራሽ ምግብና ቁሳቁስ እያሰራጨ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ልማት ማህበር በአሜሪካ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አባቶችና ምዕመናን ጋር በመተባበር በአማራ ክልሉ ጊዚያዊ መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙና በጦርነት ለተጎዱ ወገኖች የእለት ደራሽ ምግብና ቁሳቁስ በማሰራጨት ላይ ነው፡፡

አልማ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሲያትል፣ ዋሽንግተን፣ ኦሪገን አይዳሆ እና አካባቢው ከካሊፎርኒያ የአብያተ- ክርስቲያናት የሀይማኖት አባቶች፣ ምዕመናንና የሀይማኖቱ አገልጋዮች በተገኘ ከ15 ሚሊየን ብር በሚጠጋ ወጪ በደብረ ብርሀን ከተማ ለሚገኙ ተፈናቃዮችና በደቡብና ሰሜን ጎንደር፣ ዋግ ኽምራ፣ ደቡብና ሰሜን ወሎ እንዲሁም በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን በጦርነት ለተጎዱ ወገኖች ነው የዕለት ደራሽ ምግብና የትምህርት ቁሳቁስ በማጓጓዝና በማሰራጨት ላይ የሚገኘው፡፡

ከወለጋና አምቦ ተፈናቅለው ደብረ ብርሀን ጊዚያዊ መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ 7 ሺህ ተፈናቃዮች 2 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበትን የስንዴ ዱቄት ያስረከቡት በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን የሲያትል ዋሽንግተንና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ-ጳጳስ ብፅዑ አቡነ ማርቆስ ናቸው፡፡

በቀጣይም ድጋፉ ወልድያ፣ ጋይንት ፣ ከሚሴ፣ ደሴ፣ ደባርቅና ዋግ ኽምራ ለሚገኙ ተጎጂ ወገኖች የዕለት ደራሽ ምግብ የሚሰራጭ መሆናቸውንም ብፁዕ አቡነ ማርቆስ መግለፃቸውን ከአልማ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የደብረ ብርሀን ከተማ ም/ከንቲባ አቶ አከለ ወንድሙ፥ አልማ ከሀገር ውስጥና ውጭ ሀገር ከሚገኙ አባላቱና ደጋፊዎቹ የልማት ሀብት በማሰባሰብ ለሚያከናውነው ዘላቂ ልማትና የዕለት ደራሽ ድጋፍ በከተማ አስተዳደሩ ስም አመስግነዋል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version