አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐገር አቀፍ ደረጃ ብሔራዊ ምክክር ለማድረግ የሚረዳ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብር በድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ አዘጋጅነት እየተካሄደ ነው።
ኢትዮጵያ በቀጣይ ለምታደርገው ሀገራዊ ምክክር ለህብረተሰቡ ግንዛቤን ለመስጠት ታስቦ መርሃ ግብሩ መከናወኑ ነው የተገለፀው።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጀዋር፥ ሀገራዊ የምክክር መድረኩ የዜጎችን ትክክለኛ ፍላጎት የሚያንፀባረቅበት ይሆናል ብለዋል።
ይህም የዜጎች ፍላጎት ይንፀባረቅ ዘንድ ከወዲሁ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሀ ግብሮችን ማዘጋጀት አስፈላጊ ስለመሆኑ ጠቁመዋል።
የኢፌዴሪ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደአ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያን በዘላቂነት ለማሻገር ባልተግባባንባቸው ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ላይ መድረስ አስፈላጊ ስለመሆኑ አመላክተዋል።
ኢትዮጵያም በቅርብ ግዜያት ሀገራዊ ምክክር ካደረጉ ሀገራት ልምድ በመውሰድ የተራራቁ ሀሳቦችን ለማቀራረብ መስራት አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያዊያን ሀገራቸውን በመውደድ ላይ ልዩነት እንደሌላቸው ያመላከቱት አቶ ታዬ፥ ነገር ግን በጋራ የሚያኖሯቸው እሴቶች ላይ የሚታዩ ልዩነቶችን ማጥበብ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሲታዩ የነበሩ ግጭቶች የሀገሪቱ ነፀብራቅ ናቸው ያሉት ደግሞ የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዑባህ አደም ናቸው።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሀገራዊ የምክክር መድረኩን በማሳካት ረገድ የማይተካ ሚናቸውን መጫወት እንዳለባቸውም አስታውቀዋል።
በእዮናዳብ አንዱዓለም
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!