አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በመዲናዋ የኑሮ ውድነቱንና የዋጋ ንረቱን ለመቀነስ የአቅርቦት ችግርን ከመቅረፍና ህገ ወጥ አሰራሮችን ከመቆጣጠር ባለፈ የሸማች ህብረት ስራ ማህበራትን አቅም ማጠናከርና ችግሮቻቸውን መቅረፍ እንደሚገባ ተገለጸ።
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከአዲስ አበባ ህብረት ስራ ማህበበራት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው አሊ ጋር ቆይታ አድርጓል።
የሸማች ማህበራቱ ካለባቸው የአቅም ውስንነት በተጨማሪ የመጋዘን እጥረትና የተራዘመ የገበያ ሰንሰለት የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት እንዳይወጡ አድርጓቸዋል ብለዋል።
ይህንን ችግር ለመቅረፍም የከተማ አስተዳደሩ 1 ቢሊየን ብር የተዘዋዋሪ ብድር መፍቀዱ የሚበረታታ መሆኑን ጠቁመው፥ ተዘዋዋሪ ብድሩ ለግብርና ምርቶች ብቻ የሚውል በመሆኑ ለኢንደስትሪ ምርቶችም ተጨማሪ ገንዘብ ያስፈልጋል ይላሉ።
የሸማች ማህበራቱ ከአምራች ማህበራት ጋር የሚያደርጓቸው የንግድ ስምምነትም በደላሎች ጣልቃ ገብነት ምክንያት የማይከበሩ መሆናቸው አስተማማኝ አቅርቦት እንዳይኖር ማድረጉን ነግረውናል።
በሸማች ህብረት ስራ ማህበራት ሱቆች በኩል የሚፈጠሩ ህገ ወጥ ተግባራትን ለመቆጣጠርም፣ በተለይ የፍጆታ እቃዎቹ ከወጡበት የግለሰብ እጅ እስከሚገቡበት ድረስ ያለውን ሂደት ለመቆጣጠር የሚያስቸል ስርአት እየተዘረጋ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ሃላፊ አቶ አደም ኑሪ በበኩላቸው፥ የከተማ አስተዳደሩ የአቅርቦት እጥረትን ለመቅረፍና ህገ ወጥ ንግድን ለመቆጣጠር ከሚያከናውናቸው ተግባራት ባሻገር፤ የሸማች ማህበራቱ ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ለማድረግ የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህ አመት ወደ ስራ የሚገቡ አምስት የአትክልትና ፍራፍሬ የገበያ ማእከላትም ለአቅርቦት እጥረቱ መፈታት ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ ተብሎም ይጠበቃል።
የኦሮሚያ ንግድ ቢሮ በበኩሉ፥ የሸማች ህብረት ስራ ማህበራቱ ያለባቸውን የአቅም ውስንነት ለመቅረፍ እየሰራ መሆኑን ጠቁሟል።
ከመንግስት ፍቃድ ተሰጥቷቸው ያለቀረጥ ምርቶችን ከሚያስገቡ አስመጪዎች ጋርም የሸማች ህብረት ስራ ማህበራቱን የማስተሳሰር ስራ እየተሰራ መሆኑን ነው በቢሮው የመሰረታዊ ሸቀጦች ዳይሬክሩ አቶ ሊቁ በነበሩ የገለፁት።
ለአጠቃላይ የኑሮ ውድነት እንደ ምክንያት የሚጠቀስ አንድ ብቻ ጉዳይ ባለመኖሩ በተለያዩ ዘርፎች ላይ የሚገኙ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባልም ብለዋል የስራ ሃላፊዎቹ።
በትእግስት ስለሺ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!