Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የየካቲት 12 የሰማዕታት መታሰቢያ ቀን እየተከበረ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የየካቲት 12 የሰማዕታት መታሰቢያ ቀን በአዲስ አበባ ስድስት ኪሎ በሚገኘው የሰማዕታት ሀውልት እየተከበረ ነው።
በበዓሉ ስነ ስርዓት ላይ ጀግኖች አባት አርበኞች፣የአዲስ አበባ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ቡዜና አልቃድርን ጨምሮ የከተማ አስተዳደሩ የስራ ኃላፊዎች፣ የስካውት አባላት እንዲሁም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።
በ1888 ዓ/ም ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለመያዝ የጣሊያን ጦር ዘመናዊ መሳሪያን ታጥቆ ቢመጣም ባልተለመደ ሁኔታ እስከ አፍንጫው የታጠቀው ዘመናዊና ግዙፉ የአውሮፓዊት አገር የጣሊያን ጦር ብርቱ ልብ እንጂ ይኼ ነው የሚባል ዘመናዊ መሳሪያ ባልነበራቸው በጀግኖቹ የኢትዮጵያ ልጆች ተሸንፏል፡፡
ይህ ሽንፈት ለኢትዮጵያ ጊዜ የማይሽረው ታሪካዊ ድል ቢሆንም ወራሪውን ኃይል አንገት ያስደፋ የውርደትና ቅሌት ጦርነት ነበር፡፡
ከዚህ አስከፊ ውርደት ለማገገምና ኢትዮጵያን ለመበቀል በወቅቱ የጣሊያን ገዥ ቢኒቶ ሙሶሎኒ ከ40 ዓመት በኋላ ኢትዮጵያን የወረራት ሲሆን፥ ለጊዜውም ቢሆን የጦር የበላይነት አግኝቶ የተወሰኑ ከተሞችን ይዞም ነበር፡፡
ሆኖም ግን ለነፃነታቸው የማይተኙና ባርነትን የማይቀበሉ የኢትዮጵያ ልጆች ለወራሪው ኃይል የእግር እሳት ሆኑባቸው፡፡
በተለይም በየካቲት 12 ቀን 1929 ዓ/ም በአዲስ አበባ ስብሰባ ሲመራ በነበረው የፋሺሽቱ እንደራሴ የነበረው ማርሻል ሩዶልፍ ግራዚያኒ ላይ በነፃነት ታጋዮች የግድያ ሙከራ ተደረገበት፡፡
ሙከራውን ተከትሎ ድርጊቱ ያበሳጨው የፋሺሽቱ ጦር ለሦስት ተከታታይ ቀናት በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ላይ የጅምላ ጭፍጨፋ ፈፅሟል፡፡
ከ20 ሺህ እስከ 30 ሺህ የሚገመቱ ንፁሃን ዜጎች ጭካኔ በተሞላበት አኳኋን በጅምላ ጨፍጭፏል፡፡ ዕለቱም እስከ ዛሬ ድረስ የየካቲት 12 ሰማዕታት መታሰቢያ ሆኖ ይውላል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version