Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በሳዑዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ በተዘጋጀው የማስፈፀሚያ ዕቅድ ላይ ውይይት ተደረገ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሳዑዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ በተዘጋጀው የማስፈጸሚያ ዕቅድ ላይ የብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ አባላትን ያሳተፈ ውይይት ተካሄደ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በውይይቱ እንደገለጹት÷ በሳዑዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው መመለስ የሚቻልበት ሁኔታ ላይ በመወያየት ከዚህ ቀደም የታዩ ክፍተቶችን ለመቅረፍ እንዲሁም በባለድርሻ አካላት መካከል የተጠናከረ ቅንጅት እንዲኖር የጋራ ውይይቱ ፋይዳው ጎላ ነው ብለዋል፡፡
የመንግስት ተቋማት አደረጃጀት ላይ የተደረገ ለውጥ በመኖሩ ምክንያት÷ የብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴውን በአዲስ መልክ ማደራጀት ማስፈለጉን ጠቁመው÷ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተዘጋጀው ረቂቅ ዕቅድ ላይ በብሄራዊ ቴክኒክ ኮሚቴነት እንዲካተቱ ከቀረቡት ተቋማት በተጨማሪ በስራው ድርሻ ያላቸው ሌሎች ተቋማትንም በማካተት እና እያንዳንዱ ተቋም ዜጎች በመመለስ ሂደት ውስጥ የሚያከናውነውን የሥራ ድርሻ በእቅዱ በግልጽ በማመልከት ወደ ስራ ይገባል ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቆንስላ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት-ጄኔራል አቶ መስፍን ገ/ማሪም ባቀረቡት የመነሻ ዕቅድ÷ ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ ዜጎች በሳዑዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
መንግሥት ከሚከተለው ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ አኳያ ዜጎችን ወደ አገራቸው ለመመለስ ትኩረት ተሰጥቶ እየሰራ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ዜጎችን ወደ አገራቸው ለመመለስ በተደረገው ጥረት ከ40ሺህ በላይ የሚሆኑትን ዜጎችን ወደ አገር መመለስ ተችሏል መባሉን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version