አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን በምርት ዘመኑ በቂ ዝናብ ባለመገኘቱ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ከ489 ሺህ በላይ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ እህል ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የዞኑ አደጋ ስጋትና ስራ አመራር አስታወቀ፡፡
ዞኑ 72 በመቶው ቆላማ የአየር ንብረት መያዙ የድርቅ ስጋቱን ከፍ እንዳደረገው የዞኑ አደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኃላፊ አቶ ኑሬ መሀመድ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጸዋል፡፡
በዞኑ በሚገኙ 20 ወረዳዎች የድርቅ ስጋት መኖሩን ጠቁመው ፥ በአምስቱ ላይ ግን የጠነከረ ድርቅ ስለመኖሩም ነው ኃላፊው የተናገሩት፡፡
በቀጣይ ወራት ዝናቡ የማይዘንብ ከሆነ ጉርሱም፣ ባቢሌና ፈዲስ የተባሉ ወረዳዎችም በተጨማሪ ለምግብ እህል እርዳታ ሊዳረጉ እንደሚችሉም ነው ያብራሩት፡፡
ባለፈው ዓመት በቂ ዝናብ ባለመዝነቡ 448 ሺህ ዜጎች ለተረጅነት መዳረጋቸውን የጠቆሙት አቶ ኑሬ መሀመድ ፥ የዞኑ አደጋ ስጋትና ስራ አመራር ባጠናው ጥናት መሠረት የተረጂዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ስጋት አለ ብለዋል፡፡
በዞኑ 331 ሺህ ሰዎች ቀደም ባሉት ዓመታት የሴፍትኔት ተረጂ እንደነበሩ ያስታወሱት ኃላፊው፥ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ደግሞ 268 ሺህ ሰዎች መጨመራቸውን አመላክተዋል።
በተመሳሳይ 400 ሺህ እንስሳት በድርቁ ሊጠቁ እንደሚችሉ ቅድመ ግምቶች የተቀመጡ ሲሆን ፥ ለእንስሳቱ ምግብነት የሚውል 210 ሺህ ቤል (እስር) መኖ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በዚህም ለድርቁ ምላሽ ለመስጠት ከሚያስፈልገው 49 ሺህ ኩንታል እህል ውስጥ 26 ሺህ የሚሆነውን ለ129 ሺህ ዜጎች ማዳረስ ተችሏል ተብሏል።
በመሆኑም መንግስት እያደረገ ለሚገኘው ድጋፍ ግብረሰናይ ተቋማት ትብብራቸውን እንዲያሳዩም ተጠይቋል።
በእዮናዳብ አንዱዓለም
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!