አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢንተርናሽናል ዳኛ በዓምላክ ተሰማ እና በሲዳማ ቡና እግር ኳስ ቡድን መካከል ሲደረግ የነበረው የዲሲፕሊን ክስ ሂደት እልባት አግኝቷል፡፡
በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር በኅዳር 20 ቀን 2014 ዓ.ም ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሲዳማ ቡና ጨዋታ ከማድረጋቸው አንድ ቀን አስቀድሞ የሲዳማ ቡና ክለብ ለኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር እና ሥነ ስርዓት ኮሚቴ ባስገባው ደብዳቤ የዕለቱ ዳኛ በዓምላክ ተሰማ ‘የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊ በመሆናቸው ጨዋታውን በዳኝነት እንዳይመሩ’ በሚል ቅሬታ ማቅረቡ የሚታወስ ነው።
ይህንን ተከትሎ አርቢትሩ ተቃውሟቸውን በእግር ኳስ ስፖርተኞች ህጋዊ ወኪል እና የህግ አማካሪ እና ጠበቃ በሆኑት ብርሀኑ በጋሻው አማካኝነት ጉዳያቸውን ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፣ ስልጣን በተሰጠው የመንግሥት የፍትህ አካል ቅሬታቸውን ያቀረቡ ሲሆን ፌዴሬሽኑም ለቀረበለት ጉዳይ ሲመረምር ቆይቶ በሽምግልና መፍታት አስፈላጊ መሆኑን በማመን ሁለቱንም አካላት ወደ ፅህፈት ቤቱ በመጥራት አነጋግሯል።
በዚህም በዛሬው ዕለት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ፣ የፅህፈት ቤቱ አላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን፣ ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ በዓምላክ ተሰማ ፣ የህግ አማካሪው አቶ ብርሀኑ በጋሻው እንዲሁም የሲዳማ ቡና ተወካይ በተገኙበት ውይይት ተደርጓል።
በውይይቱም ላይ ሲዳማ ቡና ያቀረበው ክስ በሀሰት ስም ማጥፋት መሆኑን በመተማመን ድርጊቱ ለፌዴሬሽን በደብዳቤ ከተገለፀው በተጨማሪ፥ ለሚመለከታቸው አካላት በግልባጭ እንዲደርሳቸው በመስማማት የሲዳማ ቡና እግር ኳስ ቡድን ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ በዓምላክ ተሰማን ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን ፣ ብሔራዊ የዳኞች ኮሚቴን እና መላውን የእግር ኳስ ስፖርት ቤተሰብ ይቅርታ ጠይቋል።
ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ በዓምላክ በዓምላክ ተስማም ይቅርታውን ተቀብለው በጥሩ መንፈስ ውይይቱ መጠናቀቁን ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!