አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከአውሮፓ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ቻርልስ ሚሼል ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ፥ ከአፍሪካ ኅብረት እና ከአውሮፓ ኅብረት የጋራ ጉባኤ አስቀድሞ ከወዳጄ ፕሬዚደንት ቻርልስ ሚሼል ጋር ተገናኝተናል ብለዋል።
የአውሮፓ ኅብረት እና የኢትዮጵያን ግንኙነት፣ ቀጣናዊ እንዲሁም አህጉራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውንም ነው የገለጹት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በ6ኛው የአፍሪካ ኅብረትና የአውሮፓ ኅብረት የጋራ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ነው ቤልጂየም ብራስልስ የተገኙት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በብራስልስ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የአገሪቱ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ጉባኤው ከነገ ጀምሮ ለሁለት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን፥ የአፍሪካ ኅብረት እና የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት መሪዎች፣ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎችና ተወካዮች እንዲሁም የሁለቱ አህጉሮች የተለያዩ እንግዶች እንደሚታደሙ ይጠበቃል።
በአውሮፓ እና በአፍሪካ ኅብረት መካከል መካከል ያለውን የፖለቲካ ግንኙነት በማጠናከርና አህጉራቱን ወደ ብልፅግና ለማሸጋገር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ የአፍሪካ ኅብረት እና የአውሮፓ ኅብረት መሪዎች እንደሚመክሩም ነው የአውሮፓ ኅብረት ያወጣው መግለጫ የሚያመላክተው።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!