አዲስ አበባ፣ የካቲት 13፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢጋድ አሸማጋይነት የሚካሄደው የደቡብ ሱዳን የሽግግር መንግስት ምስረታ ነገ በጁባ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ከሱዳን ነጻነቷን ካወጀች 10 አመት ያልሞላት ደቡብ ሱዳን ነፃ ሀገር ሆና የራሷን ሰንደቅ ዓላማ በጁባ ካውለበለበች ሁለት ዓመት በኋላ በፖለቲከኞቿ መካከል የተፈጠረው ሽኩቻ ያስክተለባት ጦርነት ከባድ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ድቀት ውስጥ ከቷታል።
በሃገሪቱ የፖለቲካ ሽኩቻ ውስጥ ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ማያርዲያት እና የቀደሞው ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑት ኢኮኖሚስቱ ዶክተር ሪክ ማቻር ዋነኛ ተዋናይ ናቸው። ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር እና ዶክተር ሪክ ማቻር ከአሁን በፊት አዲስ አበባ ውስጥ ለፈረሙት ስምምነት ተገዥ መሆናቸውን ሲናገሩ ተደምጠው ነበር፤ ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት ህዝባቸውን በየጊዜው ይቅርታ ሲጠይቁም ቆይተዋል።
ዶክተር ሪክ ማቻርም ቢሆኑ አዲስ አበባ ውስጥ ለተፈረመው ስምምነት ተግባራዊነት እንደሚሰሩ በወቅቱ ተናግረው ነበር።
ሪክ ማቻር በወቅቱ የጁባን ፖለቲካዊ ቀውስ መፍትሄ የሚሰጠውን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ ከሁሉም አካላት ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ መናገራቸውም የቅርብ ትውስታ ነው። ይሁን እንጅ ሁለቱም የገቡትን ቃል ተግባራዊ ሳያደርጉ ዛሬ ተቀናቃኝ ሆነዋል፤ ለጁባ የፖለቲካ ትርምስ በአንድም ሆነ በሌላ በኩል ቀዳሚ ተዋናዮችም ናቸው። በፈረንጆቹ 2015 ነሃሴ ወር በአዲስ አበባ፣ በ2017 እንዲሁም እንደገና መስከረም ወር 2018 በሱዳን ካርቱም በተፈረመው የደቡብ ሱዳንን የሰላም ስምምነት ዳግም የማጠናከር ሂደት ሁለቱ ፖለቲከኞች ቀዳሚዎቹ ናቸው።
ከሁለቱ የጁባ የፖለቲካ ፊት አውራሪዎች ጀርባ ግን ምዕራባውያን በድልድዩ ስር ወንዙ ያልፋል እንደሚሉት ንፁሃን ዜጎች ህይወታቸውን አጥተዋል፤ ተሰደዋል አሁን ላይም ለከፋ ሰብዓዊ ቀውስ ተዳርገዋል። 5 ሚሊየን የሚሆኑ ዜጎቿ አሁን ከፊት ለፊታቸው የከፋ ረሃብ አደጋ ተጋርጦባቸዋል። ከሰሞኑ ደግሞ አውዳሚው የበረሃ አንበጣ መንጋ በሃገሪቱ ተከስቷል።
በጁባ ከሰሞኑ መንፈስ የጀመረው አዲስ የተስፋ ንፋስ
የደቡብ ሱዳን ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ዘጋቢ ጄኢል በርካታ የጁባ ነዋሪዎች የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ዶክተር ሪክ ማቻር እና ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት እያደረጉት ባለው የሰላም ድርድር ተስፋ መጣላቸውን ይናገራል።
በተለያዩ ግዛቶች ያሉ ነዋሪዎችም የድጋፍ ድምፅ እያሰሙ ሲሆን፥ የጁባ ፖለቲከኞችም አሁን ላይ ከፊታቸው አንድ ወሳኝ ሁነት ይጠብቃቸዋል። ህዝቡም ታሪካዊ ሁነት በጉጉት ቀናትን እየቀነሰና እየደመረ ምን ያህል ቀረ በሚለው የፖለቲካ ኢኮኖሚ ስሌት ውስጥ ነው።
በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስት (ኢጋድ) የሚመራው የጁባ የሰላም ሂደት ነገ ቅዳሜ የሽግግር መንግስት በመመስረት መፍትሄ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል።
ሃገራት አሁንም ይጠበቃል በሚል የተሸበቡ ናቸው። ለምን ?
የደቡብ ሱዳን የሽግግር መንግስት እንደ መስከረም 2018ቱ የካርቱም ስምምነት ቢሆን ኖሮ ባለፈው ግንቦት ወር ላይ ነበር የሚመሰረተው። ግፋ ቢል ደግሞ ባለፈው ታህሳስ 12 ተግባራዊ መሆን ነበረበት፤ የነገው ግን በኢጋድ አደራዳሪነት የተቀመጠው የመጨረሻው ቀነ ገደብ ሊሆን ይችላል እየተባለ ነው።
በእስካሁኑ የቅድመ ሽግግር መንግስት ምስረታ ሂደት ውስጥ የጁባ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የድርድር ሂደት ውጤት አልባ ካደረጉ ነጥቦች መካከል፥ የፀጥታ ሃይላት አደረጃጀት፣ የደቡብ ሱዳን ክልሎች ቁጥርና የወሰን ጉዳይ ቀዳሚው የልዩነት ምንጭ መሆኑን የኢጋድ የደቡብ ሱዳን ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ኢስማኤል ዋኢስ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ መናገራቸው ይታወሳል።
ከዚህ ባለፈም ለዚያች ሀገር የሽግግር መንግስት ምስረታ ድጋፍ ለማድረግ ቃል የተገባው ገንዘብ አለመለቀቅ ሌላኛው ችግር መሆኑንም ጠቅሰዋል። አምባሳደሩ የፕሬዚዳንት ሳልቫኪር መንግስት እና ተቀናቃኛቸው ወታደሮቻቸውን በጋራ ለማሰልጠን እና አንድ ብሄራዊ ጦር ለማቋቋም በሚደረገው ሂደት ውስጥ እስካሁን የተሳካ ከተባለ 18 ማሰልጠኛ ጣቢያዎችን እና ቦታዎችን መለየት መቻሉን አንስተዋል።
የወሰን እና የክልል ጉዳዮች መርማሪ ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ስራ ቢገባም የደረሰባቸውን ድምዳሜዎች እና ግኝቶች ግን ይፋ አላደረገም።
የህዝቡ ምሬት እና ስደት እየበዛ ዓለም አቀፍ ጫና የበረታባቸው ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ከሰሞኑ ታሪካዊ ሊባል የሚችል ውሳኔ አሳልፈዋል፤ ሲደምሩ ሲቀንሱት የነበረውን የክልል ቁጥር ብቻ ወደ ቀደመው 10 ክልሎች መልሰው ሶስት አስተዳደሮችንም ይፋ አድርገዋል። ይህ ውሳኔ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ታላቅ እፎይታን ሲሰጥ ፕሬዚዳንት ሳልቫኪርም ሙገሳ እያስተናገዱ ነው።
ኢትዮጵያውያን የደህንነት እና የዲፕሎማሲ ጉዳይ ምሁራን አዲስ አበባ ለጁባ ፖለቲካ እስካሁን የሰጠችውን ትኩረት አጠናክራ መቀጠል እንዳለባት ይመክራሉ።
ኢትዮጵያ ደቡብ ሱዳን አሁን ላይ ለደረሰችበት የሽግግር መንግስት ምስረታ የተወጣችው የዲፕሎማሲ ስራ መቋጫ ላጣው የጁባ ፖለቲካዊ ቀውስ መፍትሄ ለመስጠት ስታደርግ የነበረው እና የአሸማጋይነት ሚናዋ ትልቅ ዋጋ ሊሰጠው ይገባል ባይ ናቸው።
የካርቱም የፖለቲካ ሁነትም በጁባ ላይ ተዛማጅ ተፅእኖ ሳያሳርፍ አልቀረም፤ ፖለቲከኞች እና መለዮ ለባሾች ልዩነታቸውን ወደ ጎን በማለት ለህዝባቸው ቅድሚያ ሰጥተው መንቀሳቀሳቸው አሁን ላሉበት ፖለቲካዊ እርምጃ አብቅቷቸዋል። ሰሞነኛ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ጁባም በካርቱም ዱካ እያለፈች ይመስላል።
ፕሬዚዳንት ሳልቫኪርም ዶክተር ሪክ ማቻር ከዛሬ ጀምሮ ስልጣናቸውን ተረክበው መስራት ይችላሉ ብለዋል፤ ነገ ደግሞ ይፋዊው የሽግግር መንግስት ይፋ እንደሚሆን ተስፋ ተጥሎበታል።
የጁባ ፖለቲካዊ ቀውስ የመፍትሄ መሰናክሎች ምን ነበሩ?
ለጎረቤት ደቡብ ሱዳን የመፍትሄ አቅጣጫዎች መዛባት እና የፍላጎት ተቃርኖ እጥፋቶች ብዙ ምክንያቶችን መደርደር ይቻላል፤ ሶስት ነገሮች ግን የጁባን ፖለቲካ በቅርበት ለሚከታተል ሰው ጆሮ የሚስቡ ናቸው።
1. የሃገሪቱ ፖለቲከኞች የፍላጎት ተቃርኖ እና የጎሳ ፖለቲካ የጥቅም ሽኩቻ
2. ሃያላን ሃገራት ከነዳጅ ተኮር ፍላጎት ጋር በተያያዘ በሃገሪቱ ጉዳይ እጃቸው መርዘሙ
3. ከአሸማጋይና አደራዳሪ ጎረቤቶቿ የተወሰኑት ለግል ፍላጎታቸው ቅድሚያ የመስጠት ፍላጎት
አንዱ ከፕሬዚዳንቱ ሌላው ከተቃዋሚው ጎን የመሰለፍ የምስራቅ አፍሪካ የቆየ የእጅ አዙር ፍትጊያ ጂኦ ፖለቲካዊ ቅራኔ ነው።
ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር እና ዶክተር ሪክ ማቻር ከደቡብ ሱዳን ህዝብ አብዛኛውን ቁጥር የሚወስዱት የዲንቃ እና ኑዌር ጎሳ አባላት መሆናቸው እስካሁን ሲደራደሩ ከሃገራዊ ትልማቸው ይልቅ በየጊዜው ጎሳዊ ፍላጎታቸው በመሃል መደንቀሩ ትልቅ ጣጣ ሆኖባቸው ቆይቷል። በራሱ የጁባ ፖለቲከኞች ቁጥር በየጊዜው መበራከት እና የመንግስት ቁርጠኝነት ማነስም አንዱ መሰናክል ነው።
ከአሁን በፊት ከጣቢያችን ጋር ቆይታ ያደረጉት የደቡብ ሱዳኑ ኢንፎርሜሽን ሚኒስትር መንግስት ቁርጠኛ ቢሆንም በየቀኑ የሚፈጠሩ አዳዲስ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፍላጎት ተቃርኖ መብዛት ከባድ ራስ ምታት እየሆነብን ነው ማለታቸው የሚታወስ ነው።
በእርግጥ ይህ በሃሳብ ተቃርኖ በፍላጎት መጣረስ ሰበብ የሚፈጠሩ አዳዲስ የጁባ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለኢጋዱ ልዩ መልዕክተኛም ከባድ የቤት ስራ ፈጥረው ቆይተዋል። አምባሳደር ኢስማኤል ዋኢስ ከአሁን በፊት በተካሄዱ ጉባኤያት በአንዱ ይህን ምሬታቸውን ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ማሰማታቸው ይታወሳል።
በተቃራኒው የሁለት ፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች እና ቃል አቀባዮች ችግሩ ያለው ከቤተ መንግስት ነው ሲሉ ሃሳባቸውን አጋርተውን ነበር።
የሃያላን የፍላጎት ተቃርኖ በጁባ ሰማይ ስር
ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት ከአሁን በፊት ከፓን አፍሪካኒስቱ መፅሄት ኒው አፍሪካ ጋር ሰፋ ያለ ቃለ ምልልስ አድርገው ነበር። በዚህ ቃለ ምለልሳቸው ለሀገራቸው ፖለቲካ ውጥንቅጥ የውጭ ሃይላት የፍላጎት ተቀቃርኖ አንድ መሰናክል መሆኑን አብራርተዋል።
በተለይ የአሜሪካ እና የቻይና የውክልና ግብግብ በጁባ ነዳጅ ሃብት ላይ ደቡብ ሱዳን ነፃ ሀገር ሆና ከመመስረቷ አስቀድሞ የሱዳን መንግስት ከአሜሪካ ጋር በነበረው ቁርሾ የሱዳን የነዳጅ መተላለፊያ ቦይ እና ጎድጓዶች በአጠቃላይ መሰረተ ልማቱ በቻይና ኩባንያዎች እንዲሰሩ ስምምነት አስሯል።
ደቡብ ሱዳን እንደ ሀገር ስትመሰረት የነዳጅ ፖለቲካው ለጁባ እና ካርቱም ፖለቲከኞች ከባድ የልዩነት ነጥብ ሆኖ አሸማጋይ እንዲገባበት ማስገደዱም የሚታወስ ነው፤ ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ከመፅሄቱ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ አሜሪካ ከዶክተር ሪክ ማቻር ጋር መመሳጠሯን አንስተዋል። ዋሽንግተን ማቻርን ወደ ቤተ መንግስት በማስገባት ቻይናን ከነዳጅ ገበያው ማስወጣትና የእርሷን ኩባንያዎች በአዲሲቷ ሀገር በስፋት ማስገባት ፍላጎቷ መሆኑንም አስረድተዋል።
ይህ የነዳጅ ፖለቲካ ለበርካታ ጊዜያት ውስጥ ውስጡን ሲብላላ የቆየ ነበር፤ ሳልቫኪር መንግስታቸው ቻይናን ማባረር አይችልም ይላሉ ለዚህ ደግሞ ስምምነቱ ያደረ ሂሳብ እንዳለበት ያወሳሉ። ከጁባ አሸማጋይና አደራዳሪዎች መካከል ኡጋንዳ እና ሱዳን ያላቸው ተቃርኖ ስለመፈታቱ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፤ አንዳቸው ከመንግስት ሌላኛቸው ከተቃዋሚው ወገን የመሰለፍ የፍላጎት ተቃርኖ አላቸውና።
አቅጣጫው ወዴት እንደሚያመራ መገመት ቢከብደም፥ በእርግጥ አሁን በካርቱም ሰማይ ላይ አዲስ ንፋስ እየነፈሰ ነው። በእነዚህ መናክሎች ተሸብቦ የከረመው የኢጋድ አሸማጋይነት አሁን ምን አልባትም በትዕግስት አስጨራሽ መስመር አልፎ ፍሬ ሊያፈራ ከጫፍ የደረሰ ይመስላል።
ነገ አዲስ የሸግግር መንግስት በይፋ ይመሰረታል፤ ለዚህ ደግሞ መሪዎቹም ሆኑ ፖለቲከኞች ተስማምተዋል።
ከአሁን በፊት የነበሩ የፍላጎት ተቃርኖ መሰናክሎች ነገም በሽግግር መንግስቱ የስራ እንቅስቃሴ ላይ ላለመደርደራቸው ግን ማስተማመኛ የለም።
የታሰበው የተስፋ ጮራ ለኢትዮጵያ ያለው ፋይዳ
በጁባ ፖለቲካዊ ቀውስ ኢትዮጵያ በርካታ ጫናዎች እየደረሱባት ነው፤ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት በቅርበት የሚከታተሉ ምሁራን የእስካሁኑ የደቡብ ሱዳን ፖለቲካዊ ቀውስ በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ጫና እንዳደረሰባት ተናግረዋል።
የስደተኞች ጫና፣ የህገ ወጥ ጦር መሳሪያ ዝውውርና የጎሳ ግጭትን ይጠቅሳሉ። ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው የሽግግር መንግስት ምስረታ ለአዲስ አበባ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋልም ነው የሚሉት።
በቀዳሚነት ምጣኔ ሀብታዊ ግንኙነታቸውን ማሳደግ ይሆናል፤ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ከጁባ በርካታ ነዳጅ የማስገባት ፍላጎት ሊኖራት ይችላል።
ከዚህ ባለፈም ስምምነቱ በድንበር አካባቢ ያለውን ሰላም እና ደህንነት በማረጋገጥ ዘላቂ ሰላም እንዲኖር ከማድረጉም ባለፈ የስደተኞችን ቁጥር የመቀነስ አቅም አለው።
ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያን የአሸማጋይነት ሚና በማጉላት ዲፕሎማሲያዊ ሚናዋን ከፍ የማድረግ አቅም አለው ብለዋል። አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት ዋና መቀመጫ እንደመሆኗ የአፍሪካን ችግር በአፍሪካ ሽምግልና መፍታት የሚለውን መርህ ወደ ተሻለ አቅጣጫ እንደሚመራው በመጥቀስ።
ከእነዚህ ጠቀሜታዎች ባለፈ በደቡብ ሱዳን ፖለቲካዊ ቀውስ ሰበብ ከአዲስ አበባ ጋር የቆየ የጥቅም ተቃርኖ ያላቸው ሃይላት የእጅ አዙር ጦርነት እንዳይከፍቱ የማድረግ ሚናም ይኖረዋል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።
በጁባ ሰማይ ላይ የፈነጠቀው ተስፋ ወደ መሬት መውረድ ግን ለእነዚህ ሁሉ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታዎች ዋና ምሰሶ ነው።
በስላባት ማናዬ
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ! https://t.me/fanatelevision