Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኢትዮጵያ ለሰላም የዘረጋችውን እጅ ከግንዛቤ ያላስገባው የአሜሪካ ኤች አር 6600 የውሳኔ ሀሳብ ተቀባይነት የለውም- የዳያስፖራ አባላት

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 8፣2014 (ኤፍ.ቢ.ሲ)   ኢትዮጵያ ለሰላም የዘረጋችውን እጅ ከግንዛቤ ያላስገባው የአሜሪካ ኤች አር 6600 የውሳኔ ሀሳብ ተቀባይነት የለውም ሲሉ በአሜሪካ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የዳያስፖራ አባላት ገለጹ።
በዋሽንግተን ዲሲ የሚኖሩት አቶ ካሌብ አማረ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገልጹት፥ ምክር ቤቱ ባሳለፍነው ሣምንት ያሳለፈው ውሳኔ በኢትዮጵያ የሰላምና የዴሞክራሲ ግንባታ ለመደገፍ የሚል ስም የተሰጠው ቢሆንም ለከፋ ችግር የሚዳርግ ነው፡፡
ኤች አር 6600 ኢትዮጵያን የሚያዳክም እና በአፍሪካ ቀንድ ተጨማሪ አለመረጋጋት እንዲፈጠር የሚያደርግ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተጠያቂ የሚባሉ ግለሰቦች ላይ ማዕቀብ መጣል፣ አሜሪካ ለኢትዮጵያ ድጋፍ እንዳታደርግ ማስቆምና ከሌሎች ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እርዳታና ብድር እንዳታገኝ ክልከላ እንዲደረግ፣ እንዲሁም የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎችን ለመገደብ የተዘጋጀ ረቂቅ መሆኑ ተመላክቷል።
የውሳኔ ሀሳቡ ተግባራዊ እንዳይሆን በውጭ ከሚኖሩት ሌሎች ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራ አባላት ጋር በመሆን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤትን እስከማነጋገር ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ነው አቶ ካሌብ የገለጹት፡፡
ኢትዮጵያ የተደቀኑባትን ፈተናዎች በተባበረ የዜጎቿ ክንድ ተወጥታ ዛሬ ላይ ደርሳለች ያሉት አቶ ካሌብ፥ ወደፊትም የሚገጥሙንን መከራዎች ለመከላከል በአንድነት መንፈስ መቆም ይገባናል ብለዋል።
በአፈወርቅ አለሙ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version